Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋንግን ተቀብለው አነጋገሩ

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋንግ የተመራውን ልዑክ በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ።

ውይይታቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው በኩል፥ “የቻይና ሕዝባዊ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋንግ እንኳን ወደ ኢትዮጵያ በደኅና መጡ” ብለዋል።

የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት አሁንም ጸንቶ ቀጥሏልም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

“የዛሬው ውይይታችን ይህንን እና በልማት የምንጋራውን ስልታዊ የጋራ ዓላማ፤ እንዲሁም አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ትብብርን አጉልቶ አሳይቷልም” ነው ያሉት።

ውይይቶቹ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ስትራቴጂያዊ ትብብር እና በባለብዙ ወገን ትብብር ላይ ያተኮረ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ኢትዮጵያ እና ቻይና የጋራ የልማት አጀንዳ በመያዝ የኢኮኖሚ እና የኢንቨስትመንት ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማሳደግ እና የጋራ ተጠቃሚነታቸውን የሚያጠናክር አጋርነታቸውን ስለማስቀጠል በውይይቱ ተነስቷል፡፡

በቅርቡ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ቺን ጋንግ የአምስት የአፍሪካ ሀገራት ጉብኝትን ዛሬ በኢትዮጵያ ጀምረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.