Fana: At a Speed of Life!

ተመድ በሰብዓዊ እርዳታና በአደጋ ስጋት ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የድርቅ መከላከልና ምላሽ ማስተባበሪያ በኢትዮጵያ በሰብዓዊ እርዳታ እና በአደጋ ስጋት ጉዳዮች ላይ በቅንጅት እንደሚሰራ አስታውቋል፡፡
 
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማሪያም እና ምክትል ኮሚሽነሮች ከተመድ የድርቅ መከላከልና ምላሽ አስተባባሪ ሪና ጌላን ጋር ተወያይተዋል፡፡
 
በውይይታቸውም በኢትዮጵያ ወቅታዊ የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ፣ በዘላቂ መፍትሔዎችና የኮሚሽኑን አቅም ማጎልበት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
 
አስተባባሪሪና ጌላን በኢትዮጵያ አሁን ላይ በድርቅና በሌሎች አደጋዎች ችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች የሚደረገውን የሰብዓዊ እርዳታ አድንቀዋል፡፡
 
በተለይም ከሰላም ስምምነቱ ወዲህ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል እየተከናወነ የሚገኘው የሰብዓዊ እርዳታ እና የመልሶ ግንባታ ስራ የሚበረታታ መሆኑን አንስተዋል፡፡
 
ኢትዮጵያ ለድርቅ አና ሌሎች የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የቅድመ ማስጠንቀቂያ ጥናት በማድረግ እያከናወነች ያለው ስራም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
 
በቀጣይም ተመድ በኢትዮጵያ የአደጋ ስጋትን በመቀነስ ላይ በቅርበት እና በቅንጅት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡
 
በኢትዮጵያ በሰብዓዊ ድጋፍና በሚከሰቱ አደጋዎች ምላሽ መስጠት ላይ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ቃል መግባታቸውንም የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ ለፋና ብሮድካስቲክግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
 
በመላኩ ገድፍ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.