በኢዝላማባድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በይፋ ተመረቀ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢዝላማባድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በይፋ ተመርቋል፡፡
ኤምባሲውን መርቀው የከፈቱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ እና የፓኪስታን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሂና ራቢኒ ካሃን ናቸው።
በዚህ ወቅት አምባሳደር ምስጋኑ የኤምባሲው በይፋ መመረቅ በኢትዮጵያ እና ፓኪስታን ግንኙነት አዲስ የዲፕሎማሲ ምዕራፍ የከፈተ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን ከሁለትዮሽ ባሻገር በጋራ የሚሰሩባቸው በርካታ ዓለምአቀፍ የጋራ ጉዳዮች እንዳሉ ያስታወሱት አምባሳደር ምስጋኑ የኤምባሲው መከፈት ግንኙነቱን ለማስፋት እና ለማጠናከር ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ገልፀዋል።
የተጀመሩ የንግድ ፣ የኢንቨስትመንት እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ስራዎች እንዲጠናከሩ ኤምባሲው እንደሚሰራ በመጥቀስም፥ ግንኙነቱን አሁን ካለበት ይበልጥ ለማጎልበት የኢትዮጵያ መንግስት ቁርጠኛ መሆኑንም ተናግረዋል።
የፓኪስታን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሂና ራቢኒ ካሃን ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን ተመሳሳይ የልማት እና ኢኮኖሚ ፈተና ያለባቸው ሀገሮች መሆናቸውን በመጠቆም ለጋራ ችግር የጋራ መፍትሄን ለመፈለግ ትብብራቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው አስታውቀዋል።
አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እንደመሆኗ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኢዝላማባድ መኖር ከሁለቱ ሀገራ ባሻገር ፓኪስታን ከአፍሪካ ጋር ለሚኖራት ግንኙነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረውም ነው የተናገሩት።
በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር በበኩላቸው፥ ኤምባሲው ከአንድ አመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በይፋ ለምረቃ እንዲበቃ የፓኪስታን መንግስት ላደረገው ድጋፍ ምስጋና ማቅረባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡