በኢትዮጵያ የሚገኙ የአሜሪካ ንግድ ምክር ቤት አባላት ከፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ ጋር መከሩ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የሚገኙ የአሜሪካ ንግድ ምክር ቤት አባላት ከፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም በዋናነት በኢትዮጵያ ስላለው የንግድና ኢንቨስትመንት አመቺነትና ስላለው መልካም አጋጣሚ በሚኒስትሯ ገለጻ ተደርጎላቸዋል።
ኢትዮጵያ ከፍተኛ የማደግና የመበልጸግ ፍላጎትና እቅድ አላትና ለዚህም ስኬት በርካታ አስቻይ እድሎች ያሉባት ሀገር መሆኗን አንስተዋል።
ግብርና፣ ማዕድን፣ ማምረቻ፣ ግብርና ማቀነባበርና ሌሎች ከአገልግሎትና ከቱሪዝም ጋር የተገናኙ የኢንቨስትመንት ሰፊ እድሎችን የያዘችና በርካታ ማበረታቻዎችን ለባለሃብቶች በማመቻቸት ላይ ያለች ሀገር ስለመሆኗ አብራርተዋል።
ለአልሚ የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች የተዘጋጁ የኢንቨስትመንት ፓርኮች ተገንብተው በአገልግሎት ላይ መሆናቸውንም ነው ያነሱት፡፡
መንግስት የግሉን ዘርፍ ለመደገፍና በኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን ድርሻ ለማሳደግ ፖሊሲዎችን ከማሻሻል ጀምሮ በርካታ ሪፎርሞችን እያደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።
ኩባንያዎቹ ሌሎች የአሜሪካ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡና እንዲያለሙ በማድረግ ረገድ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጠይቀዋል።
በተጨማሪም ኩባንያዎቹ ፥ ከንግድ፣ ከኢንቨስትመንትና ከታክስ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን ያቀረቡ ሲሆን ሚኒስትሯ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የንግድ ምክርቤቱ አባል ኩባንያዎችም ያላቸውን ኢንቨስትመንት ለማሳደግና ተጨማሪ ባለሃብቶችና ኩባንያዎች መጥተው እንዲሰሩ ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡