አቶ ደመቀ መኮንን ከቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 17 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋንግ ጋር ተወያዩ።
ሚኒስትሮቹ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል።
በውይይታቸው ወቅት አቶ ደመቀ መኮንን በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።
ቻይና የኢትዮጵያ ትልቋ የንግድ አጋርና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ምንጭ መሆኗን ያነሱት አቶ ደመቀ፥ ቤጂንግ በኢትዮጵያ የወደፊት እድገት ላይ ትልቅ አበርክቶ እንዳላት አስገንዝበዋል።
አያይዘውም የቻይና ህዝብና መንግስት ለምስራቅ አፍሪካ ብሎም ለአፍሪካ ቋሚ አጋር መሆናቸውን አረጋግጠዋልም ነው ያሉት።
የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋንግ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የቻይና ታማኝ አጋር መሆኗን በማውሳት፥ ሀገራቸው ወደ ተሻለ እድገት ለመድረስ ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
ሚኒስትሩ በንግግራቸው በኢኮኖሚው ዘርፍ በተለይም በንግድ እና ኢንቨስትመንት ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር እድሎች መኖራቸውን አስረድተዋል።
ሚኒስትሮቹ በውይይታቸው በባለብዙ ወገን መድረኮች ላይ የጋራ በሆኑ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ አወንታዊና ገንቢ ሚና ለመጫወት በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል።
አቶ ደመቀ መኮንን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ግብዣ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት በትናንትናው ዕለት ቤጂንግ መግባታቸው ይታወሳል።
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!