ኢትዮጵያ የሥነ-ሕዝብና ተያያዥ የልማት ጉዳዮችን በልማት እቅዶቿ ውስጥ አካታ እየተገበረች ነው- አቶ ሳንዶካን ደበበ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የሥነ-ሕዝብና ተያያዥ የልማት ጉዳዮችን በልማት እቅዶቿ ውስጥ አካታ እየተገበረች መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የዓለም ሥነ-ሕዝብ የ2023 ዓመታዊ ሪፖርት በኢትዮጵያ ይፋ ተደርጓል፡፡
ሪፖርቱ 8 ቢሊየን ህይወት፣ ማለቂያ የሌላቸው አማራጮች የመብትና የምርጫ ጉዳይ በሚል ርዕስ በተዘጋጀ መርሐ ግብር ላይ ነው ይፋ የሆነው፡፡
በመርሐ ግብሩ የተገኙት የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሳንዶካን ደበበ እንደገለጹት÷ ኢትዮጵያ ከ100 ሚሊየን በላይ የህዝብ ቁጥር ካላቸው 14 የዓለም ሀገራት መካከል አንዷ ናት፡፡
መንግስት የሕዝብ ቁጥር የሚያመጣውን መልካም እድልና ተግዳሮት ጠንቅቆ ይረዳል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው÷ የ10 ዓመቱ እቅድ ከዘላቂ የልማት ግቦችና ከአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ተደርጓል ብለዋል፡፡
የሥነ-ሕዝብና ተያያዥ የልማት ጉዳዮችን ኢትዮጵያ በልማት እቅዶቿ ውስጥ አካታ እየተገበረች መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ስለ ሥነ-ሕዝብ ጉዳይ መወያየት ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱን ሰው በተለይም የሴቶችና ህጻናትን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባም አንስተዋል፡፡
የሥነ-ሕዝብ ፖሊሲ መከለስን ጨምሮ ሌሎች ተግባራትን ከልማት አጋሮች ጋር በቅንጅት እየተተገበሩ እንደሆነ መጠቆማቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
በመድረኩ የተባበሩት መንግስታት የሥነ-ሕዝብ ፈንድ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ኮፊ ካውሜ፣ የዓለም አቀፉ የስደተኞች ተቋም የኢትዮጵያ ዳይሬክተርና የተባበሩት መንግስታት ተወካይ አቢባቱ ዋኔ ተሳትፈዋል፡፡