Fana: At a Speed of Life!

አቶ ደመቀ መኮንን በቻይና ያደረጉት ጉብኝት የሁለቱን አገራት ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረ ነው – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በቻይና ያደረጉት ጉብኝት የሁለቱን አገራት ትብብርና ወዳጅነት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ።
 
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ዛሬ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ÷የአቶ ደመቀ መኮንን የአምስት ቀናት የቻይና ጉብኝት ውጤታማ መሆኑን ገልፀዋል።
 
አምባሳደር መለስ ዓለም÷ በጉብኝቱ ቻይና የኢትዮጵያ ሁነኛ አጋር አገር እንደሆነች እና በቀጣይም በፖለቲካና ዲፕሎማሲ መስኮች የተሻለ ወዳጅነት ለመመስረት የሚያስችል መግባባት ላይ መደረሱን ገልፀዋል።
 
ከአገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ከጉዋንዱንግ ግዛት አስተዳደሮች ከጉዋንዡ ከተማ ከንቲባ ጋር ጥሩ ውይይት መካሄዱንም አንስተዋል።
 
በአህጉራዊ የአፍሪካ ቀንድን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ያለንን ትብብር ለማስፋትም መረዳዳት ተችሏል ብለዋል።
 
ጉዋንዡ 300 ኩባንያዋች ተሳታፊ የሆኑበት የኢንቨስትመንት ስኬታማ ውይይት መካሄዱን እና አዳዲስ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ በመግባት በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ፍላጎት ማሳየታቸውን ቃል አቀባዩ ገልፀዋል።
 
በቻይና መዲና ቤጂንግ ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ የተሰራው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለአገልግሎት መብቃቱንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.