Fana: At a Speed of Life!

የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች በትግራይና በአማራ ክልል በመሪዎች ደረጃ የተጀመረው ግንኙነት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ለማፋጠን እንደሚረዳ ገለጹ

 

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)በትግራይና በአማራ ክልል በመሪዎች ደረጃ የተጀመረው ግንኙነት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ለማፋጠን ይረዳል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕስ መስተዳደር የተመራ የሥራ ኃላፊዎች ቡድን ከትናንት በስትያ በአማራ ክልል ባህርዳር ከተማ ከተለያዩ የህብረተሰብ ተወካዮች ጋር መወያየቱ ይታወሳል።

በውይይቱም የሁሉቱ ክልሎች ርዕስ መስተዳድሮች የሁለቱን ሕዝቦች የእርስ በርስ ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት በሁለቱ ክልሎች መሪዎች የተጀመረው መልካም ግንኙነት መጠናከር አለበት ብለዋል።

ግኑኝነቱ የሰላም ስምምነት ዘላቂ እንዲሆን እና ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

ከመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች አቶ በየነ ይልማ በሰጡት አስተያየት÷ የአማራ እና የትግራይ ክልሎች ግንኙነት መጠናከር ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ ያስችላል ብለዋል።

ለኢትዮጵያ ህዝብ ዘላቂ ሰላምና ደህንነት፤ ልማትና አድገት መረጋገጥም የላቀ ፋይዳ ስላለው እንደሚደግፉትም አረጋግጠዋል።

በሁለቱ ክልሎች ርዕሰ መስተዳደሮች ደረጃ የተጀመረው ግንኙነት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙት ለማፋጠን ያግዛል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

መምህርት ኪዳን አርዓያም በበኩላቸው÷ የሁለቱ ክልልች ርዕስ መስተዳደሮች ግንኙነት የሰላም ስምምነቱን እንዲጸና የሚያግዝ ነው ብለዋል።
”የተጀመረው ግንኙነት እየተመካከርን እና እየተጋገዝን ችግሮቻችንን እየፈታን ለጋራ እድገት እንድንተጋ ያደርጋናል” ሲሉም መናገራቸውም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የሁለቱ ክልሎች መሪዎች ያለፈው ጥፋት ይብቃ ብለው የህዝባቸውን ፍላጎት ለመፈጸም እንቅስቃሴ መጀመራቸው የሚደገፍ ተግባር መሆኑንም ገልጸዋል።

”የሁለቱ ክልሎች ርዕሰ መስተዳደሮች የጀመሩትን መልካም ግኑኝነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሻገር ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል” ያሉት ደግሞ መርጌታ ካሳ ያሬድ ናቸው።

በግጭቱ ምክንያት በሕዝቦች ላይ የደረሰው የስነ-ልቦና፣ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና እንዲወገድ የተጀመረው ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በሁሉም መደገፍ አለበት ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.