ድንበር ተሻጋሪ የታዳሽ ኃይል ፕሮጀክቶች ቀጣናዊ ውኅደት ያጎለብታሉ – ዊሊያም ሩቶ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ድንበር ተሻጋሪ ታዳሽ የዘላቂ ኃይል የመሠረተ-ልማት ፕሮጀክቶች የኃይል ንግድን ከማሳለጥ ባለፈ ቀጣናዊ ውኅደትን እንደሚያጎለብቱ የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ገለጹ፡፡
የአፍሪካን የዘላቂ ኃይል አማራጭ ፎረም የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ናይሮቢ በሚገኘው ኬንያታ ዓለም አቀፍ የስብሰባ ማዕከል ተገኝተው በይፋ አስጀምረዋል፡፡
ዊሊያም ሩቶ ÷ ቀጣናዊ የዘላቂ ኃይል አማራጭ ትብብር በጣም አሥፈላጊ መሆኑን ጠቁመው የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥም በጋራ ለመሥራት እንነሳ ብለዋል፡፡
በመድረኩ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የታዳሽ ኃይል አቅም ታቀርባለች ተብሏል፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሐብታሙ ኢተፋ (ዶ.ር/ኢ.ር) ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ልማት ላይ እያከናወነች ያለችውን ሥራዎችም እንደምታጋራ ተመልክቷል፡፡
የኬንያው ፕሬዚዳንት በመክፈቻ ንግግራቸው እንዳሉት ፥ የሕዝብ ተቋማት ወደ ንጹህ እና ዘላቂ የኃይል አማራጮች መሸጋገር አለባቸው፡፡
ሽግግሩ የአካባቢ ጥበቃ ላይ የሚደረገውን ርብርብ ያፋጥናልም ነው ያሉት፡፡
የንጹሕ የኃይል አማራጭ ፖሊሲ ቅድሚያ የሚሰጠው እና የወቅቱ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ መሆኑን አስታውሰዋል።
በዘላቂ የኃይል አማራጭ ላይ መዋዕለ-ንዋይ ማፍሰስ የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት የምንወጣው ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን ሐብቷን በፍትሃዊ መንገድ የምትጠቀም የበለጸገች አፍሪካን ዕውን ለማድረግ የሚያስችል አማራጭ ነውም ብለዋል፡፡
ዊሊያም ሩቶ ÷ ምንም እንኳን አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ የምታበረክተው አስተዋፅዖ እዚህ ግባ የማይባል ቢሆንም የአሉታዊ ተፅዕኖው ግን እኩል ገፈት ቀማሽ በመሆኗ ተፅዕኖውን ለመግታት በአንድነት እንነሳ ሲሉም ነው በፎረሙ ጥሪያቸውን ያቀረቡት፡፡