ብሄራዊ ጥቅም ማስጠበቅ የሚያስችል የዲፕሎማሲ አቅጣጫ መከተል ያስፈልጋል- አቶ ደመቀ መኮንን
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)አለም አቀፋዊና ቀጠናዊ ሁኔታን በመገንዘብ ብሄራዊ ጥቅም ማስጠበቅ የሚያስችል የዲፕሎማሲ አቅጣጫ መከተል ያስፈልጋል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ተናገሩ፡፡
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ÷አለም አቀፋዊና ቀጠናዊ ሁኔታን በመገንዘብ ብሄራዊ ጥቅም ማስጠበቅ የሚያስችል የዲፕሎማሲ አቅጣጫ መከተል ያስፈልጋል ብለዋል።
መድረኩ የዲፕሎማሲ ስራዎች ላይ ምክክር ለማድረግ የሚያስችል ነው፤ ይህ የመጀመሪያው የምክክር መድረክ ቢሆንም፣ በቀጣይ በየአመቱ የሚካሄድ ይሆናል ሲሉም አቶ ደመቀ ተናግረዋል።
የምክክር መድረኩ አሁን ያለውን አለም አቀፋዊና ቀጠናዊ ሁኔታን ከመቼውም በላይ በመገንዘብ የሀገራችንን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ፣ ወዳጅ ለማብዛትና በአለም አቀፍ መድረኮ ላይ ተደማጭነት ለምብዛት ይጠቅማል ሲሉም ገልጸዋል።
ያለፉት ሁለትና ሶስት አመታት በዲፕሎማሲው ዘርፍ እጅግ ጫና የበዛበት ነበር ያሉት አቶ ደመቀ በዲፕሎማቶችና በህዝቡ ታታሪነት መስመር ሳንለቅ ቀይተናል ፤ይሁን እንጂ አሁንም የተለያዩ ጫናዎች መኖራቸውን መጠቆማቸውን ኢፕድ ዘግቧል፡፡
በምክክሩ ላይ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ አምባሳደሮች፣ አንጋፋ ዲፕሎማቶች፣ ተመራማሪዎችና ምሁራን ተገኝተዋል።