ዒድ አል አድሃ በዓል በደሴ እና ወልዲያ ከተሞች ተከበረ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 1 ሺህ 444ኛው የዒድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል በደሴ እና ወልዲያ ከተሞች ተከብሯል፡፡
በዓሉ በርካታ የእስልምና እምነትተከታዮች በተገኙበት ነው በሶላት ስነ-ስርዓት የተከበረው፡፡
በስነ-ስርዓቱ ላይ ተክቢራን ጨምሮ የተለያዩ ሃይማኖታዊ ስነ-ስርዓቶችም ተከናውነዋል፡፡
የደሴ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ ÷ በደሴ ከተማ የአረፋ ሰላት በሚሰግድበት ፉርቃን መስጅድ ተገኝተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
አቶ ሳሙኤል በመልዕክታቸው÷ ሙስሊሙ ማህበረሰቡ በዓሉን በመረዳዳትና በመተጋገዝ ሊያሳልፍ ይገባል ብለዋል።
ህዝበ ሙስሊሙ ከሚጠይቃቸው ጥያቄዎች መካከል የመስገጃ ቦታ እጥረት አንዱ መሆኑን ገልጸው÷ ችግሩን ለመፍታት ይሰራል ብለዋል።
በተመሳሳይ የዒድ አል አድሃ (ዓረፋ) በዓል በባህርዳር፣ በደብረ ብርሃን እና ሞጣ ከተሞች በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስነ-ስርዓቶች ተከብሯል፡፡
በከድር መሀመድ