Fana: At a Speed of Life!

ፍርድ ቤቱ 20 ተጠርጣሪዎች ላይ የተመሰረተውን የሽብር ወንጀል ክስ በዝርዝር ንባብ አሰማ

 

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የፀረ ሽብርና የህገመንግስት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በእነ መላክ ምሳሌ መዝገብ የተካተቱ ተከሳሾች በሰኔ 22 ቀን 2015ዓ.ም በነበረ ቀጠሮ በተከሳሽ ጠበቆችና በዐቃቤ ህግ በኩል የተነሱ አራት የመከራከሪያ ነጥቦች መርምሮ ብይን ከሰጠ በኃላ የክስ ዝርዝር በንባብ አሰምቷል።

በዚህም ተከሳሾቹ ጠበቆች ከሰኔ 16 እስከ ሰኔ 19 ቀን 2015ዓ.ም ድረስ የተሰጠን ዋስትና መብት ተጥሶ ያለአግባብ ለስር ተዳርገዋል ይጣራልን በማለት ባቀረቡት አቤቱታ እና የዐቃቤ ህግን መከራከሪያ ነጥብ መርምሯል።

በዚህም ያለአግባብ ለስር ተዳርገዋል የሚል አቤቱታ ከዚህ በፊት ለጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርቦ እንደነበርና ችሎቱም አለአግባብ የታሰሩበትን ምክንያት ለማጣራት ባደረገው ጥረት ክስ በመመስረቱ ምክንያት መሆኑን እና ዐቃቤህግ ዋስትናው ላይ እግድ በማስጣሉ ምክንያት መሆኑን ለመረዳት መቻላቸውን ገልጸዋል።

ይሁንና ዐቃቤ ህግ ግን በመዝገቦቹ ላይ ይግባኝ ጠይቆ አስጥያለው ያለውን እግድ ግን አለመያያዙን ማረጋገጣቸውን ጠቅሰው ዐቃቤ ህግ ከመዝገቡ ጋር እግዱን እንዲያያይዝ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

በተጨማሪም ተከሳሾቹ ከዚህ በፊት ደረሰብን ያሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲጣራላቸው በ20 ገጽ ባቀረቡት አቤቱታ ላይ ትዕዛዝ ምንደረጃ ደረሰ ሲሉ የቀረቡት ጥያቄን ተከትሎ ዐቃቤ ህግ ጥያቄው መስተናገድ ያለበት በጊዜ ቀጠሮ ችሎት መሆን እንዳለበት ጠቅሶ ይህ መደበኛ ችሎት ይህን አቤቱታ ላይ ትዕዛዝ የመስጠት ስልጣን የለውም በሚል ያቀረበው መከራከሪያ ነጥብን በሚመለከት ፍርድ ቤቱ ጥሰት ተፈጽሟል ወይስ አልተፈጸመም የሚለውን ጉዳይ እንዲጣራ የማዘዝ ስልጣን እንዳለው ጠቅሶ የተጠርጣሪዎች ጥያቄ የህግ አግባብ አለው በማለት የዐቃቤ ህግ መከራከሪያን እንዳልተቀበለው አብራርቶ ብይን ሰጥቷል።

በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ 20ኛ ተከሳሽ አንዱአለም አሻግሬ ወደ አሜሪካ ለመሄድ ዲቪ ሞልቶ እንደደረሰው ጠቅሶ ፓስፖርት ለማደስና ወደ አሜሪካ ኤምባሲ ሄዶ ጉዳይ ለመፈጸም እንዲችል እንዲታዘዝለት ባቀረበው ጥያቄን ተከትሎ ዐቃቤ ህግ የአሜሪካ ኤምባሲ የሌላ ሀገር ዲፕሎማቶች የሚኖሩበትና የሌላ ሀገር ሉአላዊ ክልል መሆኑን ተከትሎ አጃቢ ፖሊስ መሳሪያ ይዞ እንደማይገባ በመጥቀስ ፣ ተከሳሹ ገብቶ አልወጣም ሊል ይችላል በማለት ባቀረበው መከራከሪያን መመርመሩን ገልጿል።

በዚህም ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ ማንነቱ ባልተረጋገጠበትና ክሱ ባልተነበበት እንዲሁም በክሱ ላይ ዋስትና ይፈቀድለት ወይም አይፈቀድለት የሚለው ባልተረጋገጠበት ሁኔታ ላይ የተጠየቀው ጥያቄን ለጊዜው አለመቀበሉን ጠቅሶ ብይን ሰጥቷል።

በሌላ በኩል ዐቃቤ ህግ የፖሊስ ጊዜያዊ መረፊያ ምቹ አለመሆኑን ጠቅሶ ተከሳቹ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ በማለት ባቀረበው ጥያቄ መነሻ ተከሳሾቹ ያሉበት ማረፊያ ቤት ከቤተሰብ ጋር ለመገናኘት እንደሚመቻች ጠቅሰው ባሉበት እንዲቆዩ ያቀረቡትን ጥያቄ በሚመለከት ፍርድ ቤቱ መርምሮ የተከሳሾች ማንነት ባልተረጋገጠበትና ክሱ ባልተሰማበት ሁኔታ ላይ የቀረበ ማረሚያ ቤት ይውረዱ ጥያቄን አለመቀበሉን ጠቅሶ ወደፊት ትዕዛዝ እስኪሰጥ ድረስ ባሉበት እንዲቆዩ ብይን ሰጥቷል።

ከዚህ ብይን በኋላ ችሎቱ በዐቃቤ ህግ የቀረበውን የሽብር ክስ ዝርዝርን በንባብ አሰምቷል።

በዚህ ባሰማው ክስ ዝርዝር ላይ ተከሳሾቹ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ዓላማን ለማሳካት በአካል በመገናኘት በመደራጀትና በመወያየት እንዲሁም በመጋቢት ወር 2015 ዓ.ም “በዋትስአፕ” በየነመረብ መገናኛ ዘዴ ላይ ዕቁብ የሚል ስም የተሰጠው መወያያ በመክፈት በጋራ በቡድን በመወያየት፣ የአማራ ብልፅግና፣ ህወሃትና የኦሮሞ ብልፅግና ጠላቶቻችን ስለሆኑ በሃይል እርምጃ መጥፋት አለባቸው የሚል ስምምነት መድረስ፣እና ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ የትግል ሰነድ ማዘጋጀት፣ ሰነዱ ላይ ውይይት አድርጎ በማዳበር 5ቱ የአማራ አናብስቶች ንቅናቄ የተባለ ህቡዕ ድርጅት መመስረት፣ለድርጅቱ ፋይናንስ ማፈላለግ እንዲሁም የሃይል ጥቃት የሚጀመርበት ስፍራ መምረጥ እንዳለባቸው ስምምነት ላይ ደርሰዋል በማለት ዐቃቤ ህግ በክሱ ላይ ማስፈሩን ችሎቱ በንባብ አሰምቷል።

በተጨማሪም በተዘጋጀ ሰነድ ላይ ጉባኤ ለማካሄድ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደ/ብርሃን ቦራና ማርያም ዋሻ የሚባል ገዳም ምቹ መሆኑን አባላት ልኮ በማረጋገጥ፣ ህዝባዊ አመፅ ለማስነሳት፣በአመፁ መሳሪያ የታጠቁ አካላትን በማስገባት ጥቃት ለማድረስ፣ ፋኖ ከአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ በኩል እንዴት ወደ አዲስ አበባ በመግባትና በሲቪል አደረጃጀት የተነሳሳውን ህዝባዊ አመፅ ሽፋን በማድረግ ፣አ/አ ከተማ ውስጥ ጥቃት በመፈጸም ወደ ቤተመንግስት እንዴት መግባት እንደሚቻል እቅድ ማዘጋጀት የሚሉ ነጥቦች በክሱ መስፈራቸው በችሎቱ ተሰምቷል።

በዚህ መልኩ ህዝባዊ አመፅ በማስነሳት ወደ ቤተመንግስት አቅጣጫ በሚያልፉበት አካባቢ ባለ ፖሊስ ጣቢያ፣ ነዳጅ ማደያ ፣የመንግስት ተቋማትን ማቃጠልና በአስፓልት ላይ ጎማ በማቃጠል ጉዳት እንዲደርስ እንዲደረግና መንግስት መከላከል እንዳይችል አቅጣጫ አስቀምጦ መስማማት የሚሉ ዝርዝሮች በክሱ ጭብጥ ላይ መካተታቸውን ችሎቱ በንባብ አሰምቷል።

እንደ አጠቃላይ በሚያዚያ 23 ቀን 2015 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 8:00 ሲሆን አ/አ መገናኛ አካባቢ መተባበር ህንጻ 4ኛ ፎቅ ላይ የህቡዕ አደረጃጀት አባላትና አመራሮች ህዝባዊ አመፅ ማስነሳትን መሰረት ያደረገ ስብሰባ በማካሄድና የታጠቀ የሰው ኃይል መዘጋጀቱን በመግለጽ፣ የውሃ ልክ፣አሸዋ፣ሲሚንቶ፣ ግንበኛ፣ የሚል መጠሪያ ኮድ በመሰጣጣት ፣ ገንዘብ ማሰባሰብ፣ የጦር መሳሪያ እና ለወታደራዊ ምግብ ግዢ ለማዋል መዘጋጀት፣ ህዝቡን ለማሸበርና መንግስትን ለማስገደድ በማሰብ የሽብር ድርጊት ለመፈጸም ዝግጅት ሲያደርጉ ነበር በማለት ዐቃቤ ህግ በክሱ ላይ የተሳትፎ ደረጃ ጠቅሶ በዝርዝር ክስ መመስረቱን ችሎቱ በንባብ አሰምቷል።

ክሱ በችሎት ከተሰማ በኃላ በተከሳሽ ጠበቆች በኩል በተከሳሾች ላይ የቀረበው የሽብር ወንጀል አንቀጽ ዋስትና እንደማያስከለክል በመግለፅ ፣ተከሳሾቹ ቋሚ አድራሻ እንዳላቸው፣የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውን እንዲሁም ከዚህ በፊት መንግስት በጠራው የህግ ማስከበር ጥሪ ላይ በመሳተፍ ተሸላሚ የሆኑና አስተዋጽዖ ያበረከቱ ተከሳሾች መኖራቸውን እንዲሁም ለተለያዩ ተፈናቃዮች ድጋፍ ያደረጉ ተከሳሾች መኖራቸውን ጠቅሰው የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ተጠይቋል።

በዐቃቤ ህግ ተከሳሾቹ ቋሚ አድራሻ እንደሌላቸው በመግለጽ፣ ቢወጡ በስራቸው ካደራጇቸው ቡድኖች ጋር በመቀላቀል በተመሳሳይ የሽብር ተግባር ሊፈጽሙ ይችላሉ በማለት የዋስትና ጥያቄያቸውን በመቃወም ተከራክሯል።

አጠቃላይ ዋስትና መብትን በሚመለከት ሰፊ የግራ ቀኝ ክርክሮችን የተከታተለው ችሎቱ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለሀምሌ 6 ቀን 2015 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.