አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከአዘርባጃን የፐብሊክ ሰርቪስ እና ሶሻል ኢኖቬሽን ሚኒስትር ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከአዘርባጃን የፐብሊክ ሰርቪስ እና ሶሻል ኢኖቬሽን ሚኒስትር ኡልቪ ሜዲዬቭ ጋር ተወያዩ፡፡
በውይይቱ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ የአዘርባጃን መንግስት በህዝብ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ለመስራት ያለውን ፍላጎት አድንቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ እያካሄደ ያለውን ሁለገብ ማሻሻያ ለማሳደግ ከአዘርባጃን ልምድ ለመቅሰም ፍላጎት እንዳለውም ሚኒስትር ዴኤታው ገልፀዋል፡፡
የአዘርባጃን የፐብሊክ ሰርቪስ እና ሶሻል ኢኖቬሽን ሚኒስትር ኡልቪ ሜዲዬቭ በበኩላቸው ÷በሀገራቱ የጋራ ፍላጎቶች በሆኑ እንደ ፐብሊክ ሰርቪስ አቅርቦት እንዲሁም በልማት ድጋፍ፣ በትምህርት፣ በቱሪዝም እና በባህል ትስስር ዙሪያ መንግሥታቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ትብብር ለማሳደግ ያለውን ዝግጁነት መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።