Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል ከቱሪዝም ዘርፍ 9 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል በ2015 በጀት ዓመት ከቱሪዝም ዘርፍ ከ9 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን የክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል፡፡

በቢሮው የእቅድና ክትትል ዳይሬክተር ኦላና ተሾመ እንደገለጹት÷ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የመስህብ ስፍራዎችን እና መዳረሻዎችን በማስፋትና በማስተዋወቅ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ በቅንጅት ተሰርቷል፡፡

ከውጭ ጎብኚዎች የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት እና በርካታ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር በትኩረት መሰራቱንም ተናግረዋል፡፡

የመስሕብ ስፍራዎችን ከማጠናከር እና ተወዳዳሪነታቸውን ከማሳደግ ረገድ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውንም አንስተዋል፡፡

በዚህ መሰረትም በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት በደረሰባቸው የቱሪስት መስሕቦች ላይ እድሳት እና ጥገና መከናወኑን  ጠቅሰዋል፡፡

በተጨማሪም በክልሉ የሚገኙ የቱሪስት መስሕቦችን በመገናኛ ብዙሃን እና በማህበራዊ ትስስር ገጾች የማስተዋወቅ ስራ መሰራቱን አስረድተዋል፡፡

በበጀት ዓመቱም 9 ነጥብ 5 ሚሊየን የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች እና ከ237 ሺህ በላይ የውጭ ዜጎች በክልሉ የሚገኙ የመስህብ ስፍራዎችን ጎብኝተዋል ነው ያሉት፡፡

ከተለያዩ የቱሪዝም አገልግሎቶችም ከ9 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን አስረድተዋል።

በቀጣይም የክልሉን የቱሪዝም ዘርፍ ይበልጥ በማነቃቃት  የጎብኚዎችን ቁጥር ለመጨማር በትኩረት እንደሚሰራ አስገንዝበዋል።

 

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.