በአስቸኳይ ሙስና መከላከል ሥራ 4 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ማዳን መቻሉ ተገለጸ
አዲስ አበባ ፣ነሐሴ 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በአስቸኳይ ሙስና መከላከል ሥራዎች ከ4 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ማዳን መቻሉን የፌዴራል የሥነ-ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
በኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ በለጠ ብርሃኑ እንደገለጹት÷ በበጀት ዓመቱ የአስቸኳይ ሙስና መከላከል ክትትል በማድረግ ሙስና እንዳይፈጸም እና ሃብት እንዳይባክን የማድረግ ሥራ ተከናውኗል፡፡
ጥቆማዎችን መሰረት በማድረግም ሙስና የመፈጸም ሂደቱ እንዲቋረጥ፣ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥና ድርጊቱ ለቀጣይ ትምህርት እንዲሆን የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ መሰራቱን አንስተዋል፡፡
ለዚህም ኮሚሽኑ ቀልጣፋ የአሰራር ሥርዓት ዘርግቶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
በ2015 በጀት ዓመት በመላው ኢትዮጵያ በተከናወነ የአስቸኳይ ሙስና መከላከል ሥራም 4 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ማዳን መቻሉን አቶ በለጠ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ውስጥም 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በላይ የሚሆነው በፌዴራል ከሚገኙ ተቋማት ሊመዘበር የነበረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በቀጣይ የአስቸኳይ ሙስና መከላከል ሥራ ክትትልን የማጠናከር እና የአገልግሎት አሠጣጥ ቅልጥፍናን የማሳደግ ስራ ትኩረት እንደሚደረግበት ገልጸዋል።
በመላኩ ገድፍ