Fana: At a Speed of Life!

የትራፊክ አደጋ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በትራፊክ አደጋ የሚደርስን ጉዳት ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑን የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት አስታወቀ።

የአገልግሎቱ ምክትል ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ፈትያ ደድገባ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ÷እንደ ሀገር በትራፊክ አደጋ እየደረሰ ያለው ጥፋት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው ይህን ለመቀነስ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ባለፈው በጀት አመት በ10 ሺህ ተሽከርካሪዎች በአማካይ 28 በመቶ አደጋ እንደደረሰ ያወሱት ምክትል ስራ አስፈጻሚዋ አሁን ላይ ቁጥሩን ወደ 25 በመቶ ማድረስ ተችሏልም ነው ያሉት።

ባመዛኙም ከ5 እስከ 29 አመት የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ዜጎች በዚሁ አደጋ ከሚሞቱት ውስጥ ቀዳሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዚህም የሚደርሱ አደጋዎችን ለመቀነስ አገልግልቱ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በሀገራዊው የትምህርት ስርአት ውስጥ የመንገድ ትራፊክ ደህንነት እንዲካተትና የመማር ማስተማሩ አንዱ አካል እንዲሆን መደረጉንም ሃላፊዋ ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የትራፊክ አደጋን አስከፊነት እንዲረዳ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞች እየተደረጉ ይገኛሉ ብለዋል።

የዚህ አካል የሆነ ከነሐሴ 22 እስከ 27 ቀን 2015 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ የመንገድ ደህንነት ሳምንት ንቅናቄ መዘጋጀቱን ወይዘሮ ፈትያ አንስተዋል።

ንቅናቄው በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚካሄድ ሲሆን÷ ስለትራፊክ አደጋ አስከፊነትም ለዜጎች ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እንደሚሰራ ተመላክቷል፡፡

በህዝባዊ ንቅናቄው ላይም የተለያዩ ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ተገኝተው ህብረሰተቡን ያስተምራሉ ነው የተባለው።
በአሸብር ካሣሁን

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.