ለችግሮች ሁሉ በምክክር መፍትሄ በመሻት የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ የጋራ ሃላፊነታችን ነው – የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት
አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሚፈጠሩ ችግሮች ሁሉ በምክክር መፍትሄ በመሻት የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ የጋራ ሃላፊነታችን ሊሆን ይገባል ሲል የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ፡፡
የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ደስታ ዲንቃ÷ ለጋራ ሀገራችን የጋራ መፍትሄ የማበጀት ጉዳይ ለማንም የሚተው ሳይሆን የሁላችንንም ጥረትና ትብብር የሚጠይቅ ነው ብለዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ ገዥው ብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ ከ60 በላይ የተለያዩ የፓለቲካ ፓርቲዎችን ያቀፈ መሆኑን ጠቅሰው÷ ለሀገራዊ አንድነትና ሰላም ከምንም በላይ በጋራ መስራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
የሀገር ሉዓላዊነትንና ህልውናን የሚገዳደር ችግር ሲያጋጥም ጉዳቱ የሀገርና አጠቃላይ የህዝብ በመሆኑ ሁላችንም የመፍትሄው አካል ሆነን መገኘት አለበን ሲሉም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የሰለጠነ የውይይት ባህልን በማዳበር የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታን ማጠናከር እንደሚገባ ማስገንዘባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በመሆኑም የግጭት ምክንያቶችን በመለየትና በንግግር መፍትሄ በመሻት የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ሁሉም ዝግጁ መሆን አንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።
በምንም አጋጣሚ የሚፈጠር ችግር መፍትሄ አለው የሚሉት የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ÷ በንግግርና በይቅርታ ቅራኔዎችን በመፍታት ብሄራዊ መግባባት መፍጠር አለብን ብለዋል።
በተለያዩ የዓለም ሀገራት የነበሩ ችግሮች በዘላቂነት የተፈቱት በመነጋገር በመሆኑ በኢትዮጵያም ችግሮች ሁሉ በሃይል ሳይሆን በውይይትና በንግግር ብቻ ሊፈቱ ይገባል ነው ያሉት።