የውጭ ሀገራት የስራ ስምሪት የዜጎችን ተጠቃሚነት ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን እየተሰራ ነው – ሚኒስቴሩ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ኀገራት የስራ ስምሪት የሀገርን ፍላጎትና የዜጎችን ተጠቃሚነት ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን ከተለያዩ ኀገራት ጋር እየሰራ መሆኑን የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ገለጸ።
ሁለተኛው አህጉር አቀፍ የአፍሪካ የሰው ሃብት ልማትና የስራ እድል ፈጠራ ጉባኤ በአዲስ አበባ በመካሄድ ጀምሯል።
በመድረኩ የተገኙት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴዔታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር) እንደገለጹት÷ ከሀገር ውስጥ በተጨማሪ የውጭ ሀገራት የስራ ስምሪት ላይ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
በውጭ ሀገራት የስራ ስምሪቱ የሀገርን ፍላጎትና የዜጎችን ተጠቃሚነት ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን ከተለያዩ ሀገራት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው ብለዋል።
የጉባኤውም መዘገጃት በተለይም በውጭ ሀገራት የስራ ስምሪትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሰፊ የተሚክሮ ልወውጥ የሚደረግበት መሆኑን ገልጸዋል።
የክህሎት ልማት ኢትዮጵያ የቦርድ ሰብሳቢና የዘ-አይ ካፒታል ኢንስቲትዩት ስራ አስፈፃሚ ገመቹ ዋቅቶላ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ በውጭ ሀገራት የስራ ስምሪት ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሁኑ ሙያና ክህሎት ላይ መስራት ይገባል ብለዋል።
በመሆኑም በክህሎት ልማት ላይ ለሚደረገው ጥረት ስኬት ኢንስቲትዩቱ የበኩሉን ሚና መወጣቱን ይቀጥላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የጀርመን ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ድርጅት የኢትዮ-ጀርመን ዘላቂ የትምህርትና ስልጠና ፕሮግራም ማናጀር ላሪስ ፊቼል÷ጀርመን የቴክኒክና ሙያ ዘርፉን ለማጎልበትና በስራ እድል ፈጠራ ለኢትዮጵያ ድጋፍና ትብብሯን አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።