Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮ-ሱዳን ከፍተኛ የፖለቲካ ምክክር መድረክ በመካሄድ ላይ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)  ለሁለት ቀናት የሚካሄደው የኢትዮ ሱዳን ከፍተኛ የፖለቲካ ምክክር መድረክ ዛሬ ግንቦት 8 ቀን 2012 ዓም በአዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል ተጀምሯል።

ከፍተኛ የፖለቲካ ምክክር መድረኩ የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እና የሱዳን የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ኦማር በሽር ማኒስ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር በይፋ ተከፍቷል።

የሁለቱን ከፍተኛ ባለስልጣናት የመክፈቻ ንግግር ተከትሎ በተካሄደው ውይይት በድንበር አካባቢ ያሉ ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ መረጃ ተለዋውጧል።

እንዲሁም በሁለቱ አገራት በድንበር አካባቢ ዘላቂ ሰላምና ፀጥታን ለማስፈን በትብብር መሰራት ባለባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ትኩረት አድርጎ መክሯል።

በመቀጠልም በሁለቱ አገራት መካከል ከዚህ ቀደም የተቋቋሙት የተለያዩ የድንበር ኮሚቴዎች እና የትብብር ማዕቀፎችን አጠናክሮ ማስቀጠል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ የመከረ ሲሆን፥ በነገው እለትም ይህንኑ አጀንዳ በመቋጨት በሁለቱ ቀናት በተደረገው ምክክር የተደረሱ ስምምነቶችን ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።

በዚህ የፖለቲካ ምክክር መድረክ በኢትዮጵያ በኩል የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣  ጄኔራል አደም መሀመድ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እንዲሁም የመረጃ እና ደህንንት፣ የፌደራል ፖሊስ እና ሌሎች ከፍተኛ የጸጥታና ደህንነት ሃላፊዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

በተመሳሳይ በሱዳን ወገን የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስማ ሙሀመድ አብደላህን ጨምሮ የሱዳን የመከላከያ እና የደህንነት መስሪያ ቤት ሃላፊዎች እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ ከኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.