የ14 ዓመቱ ኢትዮጵያዊ የ2023 የታዳጊ ተመራማሪዎችን ሽልማት አሸነፈ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካ የሚኖረው የ14 ዓመቱ ኢትዮጵያዊ ሂመን በቀለ የ2023 የታዳጊ ተመራማሪዎችን ሽልማት አሸንፏል፡፡
ሂመን ሽልማቱን ያገኘው ÷ የቆዳ ካንሰርን የሚከላከል ሳሙና ፕሮጀክት በማቅረብና በሱ ደረጃ ካሉ ታዳጊ ተመራማሪዎች ጋር ተወዳድሮ በማሸነፉ ነው።
ሂመን ውድድሩን በማሸነፉ የ25 ሺህ ዶላር የተሸለመ ሲሆን÷ ‘ከፍተኛ የአሜሪካ ታዳጊ ሳይንቲስት’ የሚል ማዕረግም ተሰጥቶታል፡፡
በቀጣይም በታላላቅ ተመራማሪዎች ስር ሆኖ ከፍተኛ ስልጠና የሚያገኝበት ዕድል ይመቻችለታልም ነው የተባለው፡፡
ለቀጣይ ሳይንሳዊ ምርምሩም ሁለገብ ድጋፍ የሚያገኝበት ሁኔታ እንደሚፈጠርለት መገለጹን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት መረጃ ያመላክታል፡፡
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ሂመን ባገኘው ድል የተሰማውን ደስታ ገልጾ ÷ ሂመንን የመሳሰሉ በርካታ ታዳጊ ኢትዮጵያውያን እንዲፈጠሩ ወላጆችና የሚኖሩበት ማኅበረሰብ እያደረጉ ስላለው ጥረት አመስግኗል፡፡
ይኸው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥልም አገልግሎቱ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም ነው ያረጋገጠው፡፡