የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ቀሪ ሥራዎችን ለማፋጠን ያለመ ምክክር ተደረገ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር እና የኢንፎሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ቀሪ ሥራዎች በሚፋጠኑበት ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) የዲጂታል ኢትዮጵያ ስኬት መሰረት ይሆናሉ ተብለው በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር እየተከናወኑ ያሉ ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል፡፡
የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር ሰሎሞን ሶካ ባለፉት ሁለት ዓመታት በርብርብ እየተሠሩ የሚገኙ ፕሮጀክቶችን አብራርተዋል፡፡
ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ቁልፉ ጉዳይ በራስ አቅም የሚሠራበትን እና የቴክኖሎጂ ባለቤት የሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባም ነው ያነሱት በማብራሪያቸው፡፡
በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስኬት ባለድርሻ አካላት ያላቸውን ሃብትና እውቀት በማስተባበር ለስትራቴጂው ቀሪ ሥራዎች ርብርብ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ለማሳካት ባለድርሻ አካላት የሚያደርጉት አስተዋጸኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው÷ ኢመደአን የመሳሰሉ ቁልፍ ሚና የተሰጣቸው ተቋማት የሚያደርጉት አስትዋጽኦ ግን ልዩ ግምት የሚሰጠው ነው ብለዋል።
ተቋማቱ በቀጣይ የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች አጠናክረው እንዲቀጥሉ የቅንጅት አሰራሮችን የበለጠ ለማጎልበት የሚያስችሉ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ለመሥራት ስምምነት ላይ ተደርሷል።