ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአፋር ክልል ለሚገኙ ተባባሪ አካላት ስልጠና እየሰጠ ነው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአፋር ክልል ለሚገኙ ተባባሪ አካላት ስልጠና መስጠት ጀምሯለ፡፡
ስልጠናው በክልሉ ከሚገኙ 48 ወረዳዎች ለተውጣጡ 380 ተባባሪ አካላት ነው በሰመራ ከተማ እየተሰጠ የሚገኘው፡፡
ስልጠናው ተባባሪ አካላቱ በየወረዳቸው ከሚገኙ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍል ተወካዮች በአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ ላይ ተሳታፊዎችን በመለየት ሒደት ውስጥ ለኮሚሽኑ እገዛ እንዲያደርጉ አቅማቸውን ለማጎልበት ያለመ ነው ተብሏል፡፡
በክልሉ ኮሚሽኑ ከየማህበረሰብ ክፍሉ በአጀንዳ ማሰባሰብ ሒደት ተሳታፊዎችን ሲለይ ለኮሚሽኑ ድጋፍ እንዲያደርጉ እየሰለጠኑ የሚገኙ ተባባሪ አካላት ምልመላ የአካባቢውን ዓውድ ከግምት ያስገባ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የጎሳ መሪዎች ተወካይ፣ የሃይማኖት መሪ ተወካዮች፣ የሲቪክ ማህበራት ም/ቤት ተወካይ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ተወካይና የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ተወካይ በክልሉ የኮሚሽኑ ተባባሪ አካላት ሆነው እንደሚሰሩ ተገልጿል፡፡
ከዚህ ባለፈም የወረዳ አስተዳደር ተወካይ፣ የሸሪአ ፍርድ ቤት ዳኞች (ቃዲዎች)፣ የወረዳ ፍርድ ቤት ዳኞች እና የሀገር ሽማግሌዎች (ሱልጣኔቶች) ተባባሪ አካላት ሆነው እንደሚሰሩ የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡
ስልጠናው ለ3 ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ሲሆን÷ሰልጣኝ ተባባሪ አካላቱ ስለ ምክክር መሰረታዊ ጽንሰ ሃሳቦች፣ ስለ ኮሚሽኑ ዓላማ እና መርሆዎች እንዲሁም በተሳታፊዎች ልየታ ሒደት ላይ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች ግንዛቤን ለመፍጠር ታስቦ እየተካሄደ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡