ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የእስልምና እምነት ተከታዮች ጎበኙ
አዲስ አበባ፣ግንቦት 9፣2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ዛሬ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ መሳለሚያ እህል በረንዳ አካበቢ በመገኘት አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የእስልምና እምነት ተከታዮች ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱም የበርካታ ቤተሰብ ኃላፊነት ያለባቸውና ኑሮአቸውን በብዙ ችግር የሚመሩ እማወራዎችን ማነጋገራቸው ተገልጿል።
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በዚሁ ወቅት “እንኳን አደረሳችሁ” በማለት ለነዋሪዎቹ የበግ፣ሩዝ፣ዱቄት፣ዘይት እና ቴምር ስጦታም አበርክተዋል ነው የተባለው።
ፕሬዚዳንቷ በወቅቱም በችግር ጊዜ የመረዳዳት እና የመደጋገፍን አስፈላጊነት ያሳሰቡ ሲሆን ”ለአንድ ወቅት ብቻ ሳይሆን ጠንካራ ባህላችን እናድርገው” ብለዋል።
አያይዘውም ወቅታዊውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከልም መንግሥት የሚያወጣቸውን መመርያዎች ማክበር እንደሚያስፈልግና የህክምና ባለሙያዎችን ምክር በተጠናከረ ሁኔታ መተግበር እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በአዲስ ከተማ ከፍለ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ከአንድ ሶስተኛው በላይ ማለትም ዘጠና ስምንት ሺ የሚሆኑት በከፍተኛ ችግር ላይ ያሉና ድጋፍ የሚሹ ሆነው መለየታቸውን ከክፍለ ከተማው የተገኘው መረጃ መጠቆሙን ከፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ያገነነው መረጃ ያመለክታል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።