Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ፓኪስታን በትምህርት ዘርፍ በትብብር ለመሥራት ተወያዩ

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር ከፓኪስታን የትምህርት እና ሙያዊ ሥልጠናዎች ሚኒስትር ማዳድ ዓሊ ሲንድ ጋር ፍሬያማ ውይይት ማካሄዳቸው ተገለጸ፡፡

ሀገራቱ በትምህርቱ ዘርፍ በተለያዩ መርሐ-ግብሮች በትብብር መሥራት የሚችሉበትን ሁኔታ ለማጠናከር የመከሩ ሲሆን፤ ወደ ተግባር ለመግባትም “ጥምር ቡድን” ለመመሥረት ተስማምተዋል።

ጥምር ቡድኑ የተወያዩበትን ሐሳብ በፊርማቸው ወደ ተግባር ለመቀየር ወደሚያስችል ሥምምነት ለመቀየር ሁኔታዎችን ያመቻቻል ተብሏል፡፡

በሙያ እና ቴክኒክ ትምህርቶች ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት እንደሚገባ የፓኪስታን የትምህርት እና ሙያዊ ሥልጠናዎች ሚኒስትር ማዳድ ዓሊሲንድ ጠቁመዋል።

ሀገራቱ በዘርፉ ያላቸውን የባለሙያዎች ዕውቀት በሥልጠና በማሸጋገር ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ያላቸውን ዕምነት አስረድተዋል፡፡

አምባሳደር ጀማል በከር÷ በቀረቡት ሐሳቦች ላይ መሥማማታቸውን ገልጸው፤ ፓኪስታን ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በተለየ ሁኔታ የትምህርት ዕድል እንድታመቻችም ጠይቀዋል፡፡

የፓኪስታኑ የትምህርት እና ሙያዊ ሥልጠናዎች ሚኒስትር ማዳድ ዓሊ ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ አምባሳደሩ መጠየቃቸውን በፓኪስታን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.