Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮ ሱዳን ከፍተኛ የፖለቲካ ኮሚቴ ስብሰባ ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 10 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮ ሱዳን ከፍተኛ የፖለቲካ ኮሚቴ ስብሰባ ተጠናቀቀ።

በሁለቱ ሃገራት ጠቅላይ ሚኒስትሮች የተወከለው ከፍተኛ የፖለቲካ ኮሚቴ ስብሰባ የሃገራቱን ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው፣ በድንበር ጉዳዮች እና አዋሳኝ አካባቢዎች የጸጥታና ደህነንት ጉዳዮች ዙሪያ መክሯል።

የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የተመራ ሲሆን፥ የሱዳን የልዑካን ቡድን ደግሞ በሱዳን የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ኦማር በሽር ማኒስ ተመርቷል።

የፖለቲካ ምክክሩ በሁለቱ ሃገራት መካከል መልካም ግንኙነትን፣ ሰላምን፣ አብሮ መኖርን እና በጋራ መግባባት ላይ የተመሠረተ የረጅም ጊዜ ግንኙነቶችን በሚያጠናክር መንፈስ የተካሄደ ነው ተብሏል።

በሁለቱ ወገኖች በተደረገው ውይይት በተለይም በሁለቱ ሃገራት አዋሳኝ አካባቢዎች በየጊዜው የሚያጋጥሙ የጸጥታና የደህንነት ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት የሚያስችሉ ውይይቶች ተደርገዋል።

ከዚህ ባለፈም የሁለቱን ሃገራት የድንበር ጉዳይ በተመለከተ የህዝቦችን አብሮነትና የግንኙነቱን ታሪካዊ ዳራ ግምት ውስጥ በማስገባት ማስቀጠል የሚያስችል ውይይትም ተካሂዷል።

ውይይቱ በሁለቱ ሃገራት አዋሳኝ አካባቢዎች የሚታዩ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ህገ ወጥ የመሳሪያ ዝውውር፣ አፈና እና የመሳሰሉ ህገ ወጥ ድርጊቶችን በጋራ ለመከላከልና መፍትሄ ማስቀመጥ የሚያስችል አቅጣጫም አስቀምጧል።

በአካባቢው የሚኖሩ አርሶ አደሮች ተረጋግተው ያለምንም መስተጓጎል የእርሻ ስራቸውን መቀጠል እንዳለባቸው እንዲሁም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋለ የመጣው የደህንነት ስጋት እና የነዋሪዎችን የተረጋጋ ህይወት የሚያውኩ አዳዲስ የጸጥታ ሃይል እንቅስቃሴዎች በአፋጣኝ እንዲስተካከሉም በተደረገው ውይይት የጋራ ግንዛቤ ተይዞበታል።

የሁለቱ ሃገራት አጎራባች የአስተዳደር አካላትም በየጊዜው እየተገናኙ ልዩነቶችን በማጥበብ በጋራ የጸጥታ ጉዳዮች ላይ መምከር እንዳለባቸው መግባባት ላይ መደረሱን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ሁለቱ ወገኖች ቀጣዩን የኢትዮ ሱዳን ከፍተኛ የፖለቲካ ኮሚቴ ስብሰባ በሰኔ ወር 2012 ዓ.ም አጋማሽ በካርቱም ለማድረግ ተስማምተዋል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.