ሰንደቅ አላማችን የአባቶቻችንና የእናቶቻችን የነጻነትና የመስዋትነት ዋና መለያ ነው -ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰንደቅ አላማችን የአባቶቻችን እና የእናቶቻችን ገድል፣ የነጻነት፣ የሉዓላዊነትና የመስዋዕትነት ዋና መለያ ነው ሲሉ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡
16ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን “የሰንደቅ ዓላማችን ከፍታ ለሕብረ-ብሔራዊ አንድነታችንና ለሉዓላዊነታችን ዋስትና ነው” በሚል መሪ ሃሳብ የተከበረ ሲሆን÷ ፕሬዚዳን ሣኅለወርቅ ዘውዴ በመርሐ ግብሩ ተገኝተው መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልእክታቸውም÷ ሰንደቅ አላማችን ስለ አባቶቻችን እና እናቶቻችን ገድል፣ የነጻነት፣ የሉአላዊነትና የመስዋዕትነት ዋና መለያ ነውም ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያን ነጻነትና አንድነት ለማስጠበቅ አባቶችና እናቶች ከፍተኛ ዋጋ መክፈላቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
ለሰንደቅ አላማ ቀን ክብር የሚሰጠው ዛሬ ብቻ ሳይሆን 365 ቀናት እንደሆነ አስገንዝበው፤ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም ቦታና ጊዜ ለሰንደቅ አላማ ተገቢውን ክብር የመስጠት ግዴታ እንዳለበት አሳስበዋል።
ክብር የሚኖረው ተጠያቂነት ሲኖር መሆኑን በመግለጽ፤ ሰንደቅ አላማ ትልቁን ቦታ የሚይዝ ብሔራዊ መለያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሕጻናትና ወጣቶችን ለብሔራዊ ሰንደቅ አላማ ክብርና ፍቅር እንዲኖራቸው ማስተማር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
በመርሐ-ግብሩ ላይ ፕሬዚዳንቷን ጨምሮ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘው ተሻገር፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ ጥንታዊ ጀግኖች አርበኞች እንዲሁም ሌሎች የመንግስት የሥራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
በየሻምበል ምሕረት