Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ክልልን ሰላም ወደ ነበረበት ለመመለስ በቅንጅት ሊሰራ ይገባል – አቶ አረጋ ከበደ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልልን ሰላም ወደ ነበረበት ለመመለስ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ከፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት ሊሰራ እንደሚባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አረጋ ከበደ ገለፁ።

በባህር ዳር ከተማ ከልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡

በመድረኩ የተገኙት አቶ አረጋ ከበደ÷ በተፈጠረው ግጭት የክልሉ መሰረተ ልማት መውደሙን እና ኢኮኖሚያዊ እድገቱ ላይ አሉታዊ ጫና ማሳደሩን አንስተዋል፡፡

የህዝቡንና የክልሉን ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ የሁሉም ሃላፊነት እንደሆነመም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የክልሉን ህዝብ ጥያቄዎች እንዲፈቱ በሰላማዊ መንገድ ትግል ማድረግ እየተቻለ ክልሉን ወደ ኋላ የሚመልስ አካሄድ አግባብነት የለውም ብለዋል።

የክልሉን ሠላም ወደ ቀደመው ለመመለስ ህብረተሰቡ ከመከላከያ ሠራዊቱና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባም ገልፀዋል።

ያለ መከላከያ ሠራዊቱ ሀገር ሠላሟ ሊጠበቅና ህዝቡ ህልውናው ሊረጋገጥ ስለማይችል የሰራዊቱን ስምና ዝና የሚያጠለሹ አካላት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ ማሳሰባቸውን የክልሉ ኮሙኑኬሽን መረጃ ያመላክታል፤፤

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በበኩላቸው÷ በውይይት ላይ የተመሰረተ አማራጭን መከተል እንደሚገባና ህዝቡ የራሱን ሚና መለየትና መወጣት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

በውይይት መድረኩ በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ፣ የምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌ/ጄ መሐመድ ተሰማ፣ የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌ/ጄ ብርሀኑ በቀለን ጨምሮ ሌሎች የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.