አምባሳደር ምስጋኑ ከዓለም አቀፉ የሰላም ምርምር ኢንስቲትዩት ልዑክ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከዓለም አቀፉ የሰላም ምርምር ኢንስቲትዩት ልዑክ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ አምባሳደር ምስጋኑ÷እንደ ዓለም አቀፉ የሰላም ምርምር ኢንስቲትዩት አይነት ተቋም ጋር በሰላም እና ደህንነት ዙሪያ በትብብር መስራት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የምርምር ተቋማት ጋር በትብብር ለመስራት ፍላጎት እንዳላት የገለፁት ሚኒስትር ዴኤታው÷አጋርነቱ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያና የአፍሪካ ቀንድ ያሉበትን የሰላም ሁኔታ እንዲገነዘብ ያግዛል ብለዋል፡፡
ዓለም አቀፉ የሰላም ምርምር ኢንስቲትዩት ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ጋር በትብብር ለመስራት ያደረገውን ተነሳሽነትም አድንቀዋል።
የዓለም አቀፉ የሰላም ምርምር ኢንስቲትዩት ልዑክ መሪ ዳን ስሚዝ በበኩላቸው÷ተቋማቸው በግጭት፣ በጦር መሳሪያ፣ በጦር መሳሪያ ቁጥጥር እና ትጥቅ አፈታት ዙሪያ ምርምር የሚያደርግ ገለልተኛ ተቋም መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም ዓለም አቀፉ የሰላም ምርምር ተቋም ሰላምና ደህንነትን ለማስፈን በሚደረጉ ጥናቶች ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት ዝግጁ ነው ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡