Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ ከተማ ከስደት ተመላሾችን ተጠቃሚ የሚያርግ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 700 ከስደት ተመላሽ ኢትዮጵያውያንን ተጠቃሚ የሚያርግ ፕሮጀክት በአዲስ አበባ ከተማ ይፋ ሆነ፡፡

ፕሮጀክቱ በዩኤን ሃቢታት፣ በዓለም አቀፉ ሰራተኞች ድርጅት እና በዓለም ጤና ድርጅት የሚደገፍ ነው ተብሏል፡፡

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን በፕሮጀክቱ ይፋ ማድረጊያ ስነ ስርዓት ላይ÷ ፕሮጀክቱ ሁሉን አካታች የሆነ የስራ እድል ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት የሚደግፍ ነው ብለዋል፡፡

ከተለያዩ የዓለም ሀገራት በአስገዳጅ ሁኔታ የሚመለሱ ዜጎችን ለማቋቋም መንግስት የሚያደርገው ጥረት መደገፍ እንዳለበት ገልጸው፤ ፕሮጀክቱ የስደት ተመላሶችን  የስራ እድልን ጨምሮ በተለያየ መልኩ ተጠቃሚ እንደሚያርግ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የዓለም ሰራተኞች ድርጅት ዳይሬክተር አሌክሶ ሙሲንዶ በበኩላቸው÷ ፕሮጀክቱ ከስደት ተመላሾች መሰረታዊ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጥቅሞችን እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል፡፡

የዩኤን ሀቢታት ኢትዮጵያ ተወካይ ሀረገወይን በቀለ÷ ለስደት ተመላሾች ሁሉን አቀፍ እና ደጋፊ አካባቢን የሚፈጥር መሆኑን አንስተዋል።

በተለይ ከኢኮኖሚያ እና ከጤና ጋር የተያያዙ ድጋፎች እንደሚደረጉ ጠቁመዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ ከሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከአዲስ አበባ ከተማ ሰራተኛ እና ክህሎት ቢሮ እንዲሁም ከከተማው ፍትህ ቢሮ ጋር በትብብር የሚሰራ ነው ተብሏል።

በኤፍሬም ምትኩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.