Fana: At a Speed of Life!

ኢንጂነር ታከለ ኡማ ከቃሊቲ ቂሊንጦ እየተገነባ ያለውን የመንገድ ፕሮጀክት ጎበኙ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 21 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢንጂነር ታከለ ኡማ ከቃሊቲ ቂሊንጦ ድረስ እየተገነባ ያለውን የመንገድ ፕሮጀክት ጎብኝተዋል።

የመንገድ ፕሮጀክቱ 10 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን ከ60 ሜትር እስከ 40 ሜትር የሚደርስ ስፋት ያላቸው መንገዶችን ያካተተ ነው።

የፕርጀክቱ አፈጻጸም አሁን ላይ 63 በመቶ የደረሰ ሲሆን 6 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የመንገድ ግንባታ የመጀመሪያ የአስፋልት ንጣፍ ተጠናቋል።

በመንገድ ፕሮጀክቱ ከተካተቱ ድልድዮች መካከል የሶስት ድልድዮች ግንባታ ሲጠናቀቅ፥ 175 ሜትር እና 325 ሜትር ርዝመት ያላቸው የወንዝ መሻገሪያ ድልድዮችም ግንባታቸው በመከናወን ላይ ይገኛል ተብሏል።

በተያያዘ ኢንጂነር ታከለ ከቃሊቲ ቱሉዲምቱ ድረስ እየተገነባ ያለውን መንገድም ጎብኝተዋል።

የመንገዱ ግንባታ 50 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን በሁለቱም አቅጣጫ 4 ተሽከርካሪዎችን ማሳለፍ የሚችል እና 11 ሜትር ስፋት ያለው አካፋይ መንገድ እንዲሁም 6 ነጥብ 5 ሜትር የብስክሌት መንገድ ያካተተ ነው።

ከዚህ ባለፈም ሶስት ተደራቢ የተሽከርካሪ መጓጓዣ ድልድዮችን ያካተተ ሲሆን፥ 9 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የመንገዱ ክፍል የመጀመሪያ ደረጃ የአስፓልት ንጣፍ ተጠናቋል።

ኢንጂነር ታከለ የከተማ አስተዳደሩ የትራንስፖርት ዘርፉን ከማዘመን በተጓዳኝ ዘመናዊ መንገዶችን በመገንባት የከተማዋን የትራንስፖርት ስርአት ለማሻሻል እየሰራ ነው ብለዋል።

የመንገዱ ግንባታ የሚከናወነው የሃገሪቷ የወጪና ገቢ እቃ ማመላሻ በሆነው በኢትዮ ጅቡቲ መስመር ዋነኛ መንገድ ላይ እንደመሆኑ የወጪና ገቢ ምልልሱን በማፋጠን ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ከከንቲባ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.