የኢትዮጵያና የሶማሊላንድ ስምምነት ኢትዮጵያን ከብሪክስና ከአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ተጠቃሚ ያደርጋል – አቶ ገብረመስቀል ጫላ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያና የሶማሊላንድ መግባቢያ ሠነድ ስምምነት ኢትዮጵያን ከብሪክስና ከአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ ገለጹ።
አቶ ገብረመስቀል ጫላ÷ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች አራት ሀገራት በቅርቡ የተቀላቀሉበት ብሪክስ የዓለምን የገበያ ስርዓት ከ’ዩኒ-ፖላር’ ወደ ሁለትና ከዚያ በላይ አማራጭ ማስፋት የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ በብሪክስ እንቅስቃሴዋ ከአባል ሀገራቱ ጋር ለሚኖራት ሁለንተናዊ ትስስር በፍትሃዊ ዋጋ ወደ አባል ሀገራት በመላክ እና በማስመጣት ተጠቃሚ ለመሆን ስምምነቱ ትልቅ ትርጉም አለው ነው ያሉት።
ለአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና የሸቀጦች ታሪፍ ማቅረቧን አስታውሰው÷ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት በዚህ ረገድ የላቀ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።
በአህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና አማካኝነት ምርቶችን ለአባል ሀገራቱ በማቅረብ ለጋራ ተጠቃሚነት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር እንደሆነ መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የኢትዮጵያና ሶማሊላንድ ስምምነት ለአህጉራዊ ሁለንተናዊ ንግድና የልማት ትስስር እንዲሁም ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላም እና ደህንነት የሚገባትን ሚና እንድትወጣ የሚያስችል መሆኑ ይታመናል።
የመግባቢያ ሥምምነቱ ሒደት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ወደ ሥራ እንደሚገባም በስምምነቱ ወቅት ተገልጿል።