Fana: At a Speed of Life!

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አዋጁን የተላለፉ ከአንድ ሺህ 900 በላይ ግለሰቦች ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን የክልከላ ድንጋጌዎችን ተላልፈዋል የተባሉ ከ1 ሺህ 900 በላይ ግለሰቦች መቀጣታቸውን የክልሉ ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አስታወቀ።

የግብረ ኃይሉ አባልና  የክልሉ የጸጥታ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ኮማንደር አብዱላዚዝ መሃመድ ÷ወረርሽኙን ለመከላከል ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር   እጅ መታጠብና አለመጨባበጥ  ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው ÷ነገር ግን ግንዛቤው  እያላቸው የሚዘናጉ ሰዎች  ቁጥር አሁንም ከፍተኛ  መሆኑን ተናግረዋል ።

በዚህም በክልሉ በሻይ ቡና፣ ሆቴሎች እና ሌሎች ቦታዎች አካላዊ ርቀታቸውን ሳይጠብቁ ሲገለገሉና አገልግሎቱን ሲሰጡ የነበሩ ጨምሮ  276 ሰዎች በገንዘብ መቀጣታቸውን ጠቅሰዋል።

ትርፍ የጫኑ 770 የመለስተኛ ህዝብ ማመላለሻ፣ ባጃጅ እና ሞተር ብስክሌት አሽከርካሪዎች እያንዳንዳቸው እስከ ሶስት ሺህ ብር ቅጣት እንደተጣለባቸው አስረድተዋል።

ያልተገባ ዋጋ በመጨመር የተደረሰባቸው 448 ነጋዴዎች ደግሞ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ታይቶ እያንዳንዳቸው እስከ አራት ሺህ ብር እንደተቀጡ  አመልክተው “12 ነጋዴዎች ደግሞ ፈቃዳቸው ተሰርዟል “ብለዋል።

ሌሎች 459 ደግሞ በመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መታለፋቸውን ኮማንደር አብዱላዚዝ ገልጸዋል።

ከዚያም ባለፈ ሰርግ በማዘጋጀት  በርካታ ሰዎች እንዲታደሙ ያደረጉ አራት የመተከል ዞን ነዋሪዎች በፍርድ ቤት ውሳኔ እያንዳንዳቸው በስድስት ወራት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ የተወሰነባቸው መሆኑን አስታውቀዋል።

ከዚህም ሌላ ለአሶሳ ከተማ ህዝብ የመጣ ሰባት ኩንታል ስኳር ለግል ጥቅማቸው ያዋሉ ሁለት ግለሰቦችም እያዳንዳቸው በአስር ወራት እስራት እንዲቀጡ በፍርድ ቤት መወሰኑን ኮማንደሩ  መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.