Fana: At a Speed of Life!

መንግስት የህብረተሰቡን ጥያቄዎች ለመመለስ ዝግጁነት አለው – ለገሠ ቱሉ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት ህብረተሰቡ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ ነው ሲሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሠ ቱሉ (ዶ/ር) ገለፁ።

በአፋር ክልል አይሳኢታ ከተማ “ኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት ለዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ሀሳብ ህዝባዊ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ የተሳተፉ የአይሳኢታና አካባቢዋ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ለበርካታ ጊዜያት በአይሳኢታና አፋምቦ ወረዳዎች መካከል የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ እየፈሰሰ ጉዳት እያደረሠ በመሆኑ በፍጥነት እንዲሰራ ጠይቀዋል።

ወጣቶችን በማደራጀት በሰፋፊ እርሻዎች ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባም ተነስቷል።

ከክልል እስከ ቀበሌ ያለው የገበያ ትስስር የላላ መሆኑን አመልክተው፤ በአካባቢው የሚመረቱ ምርቶች ለግሽበት ስለተጋለጡ መፍትሄ እንዲበጅላቸው ጠይቀዋል።

ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ሚኒስትሩ፤ በከተማው የሚስተዋለውን የውሃ ችግር ለመፍታት ከሚመለከታቸው የፌዴራል ተቋማት ጋር በመመካከር መልስ እንዲያገኝ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

ከኑሮ ውድነትና ከስራ ዕድል ፈጠራ ጋር በተያያዘ ለተነሳው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ ሀገሪቷ ያሏትን ሀብቶችና ፀጋዎች በመጠቀም ምርታማነትን ማሳደግ ዋነኛ መፍትሔ መሆኑን ገልጸው፤ ያለውን እምቅ አቅም በመጠቀም ለዕድገት መነሳት ይገባል ብለዋል።

የአፋር ህዝብ የሠላም የፍቅርና የህብረ ብሔራዊነት ተምሳሌት ነው ያሉት ሚኒስትር ለገሰ (ዶ/ር)፤ ለኢትዮጵያ ሰላምና ሉዓላዊነት ህዝቡ መስዋዕትነት ሲከፍል የመጣ መሆኑን ማውሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በብልፅግና ፓርቲ የአፋር ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ኢሴ አደን በበኩላቸው፤ ህብረተሰቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ተገቢነት ያላቸው መሆኑን ገልፀው፤ በየደረጃው ምላሽ እንዲሰጥበት ይደረጋል ብለዋል።

የአይሳኢታ ከተማ መስተዳድር ከንቲባ ሐቢቦ ዓሊም የህብረተሰቡ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ምላሸ እንዲያገኝ ከክልሉና ከፌዴራል መንግስት ጋር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በክልሉ እያስቸገረ ያለው የጎርፍ አደጋን የመቀነስ ጉዳይም ትኩረት ማግኘቱን አስረድተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.