Fana: At a Speed of Life!

ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ከዩኔስኮ የትምህርት ዘርፍ ረዳት ዳይሬክተር ጀኔራል ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ከተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የትምህርት ዘርፍ ረዳት ዳይሬክተር ጀኔራል ስቴፋኒያ ጃኒኒ ጋር ተወያይተዋል፡፡

ውይይቱ የትምህርት ዘርፉን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለመደገፍ በትብብር መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)÷ የትምህርት ሥርዓቱን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለመደገፍና ለማዘመን እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን አስመልክተው ገለጻ አድርገዋል፡፡

ለአብነትም የቅድመ ምረቃ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና ኦንላይን እየተሰጠ መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡

የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሄራዊ ፈተናን ከኩረጃና ስርቆት ለመከላከል በኦንላይን ለመስጠትና ሁሉንም አይነት የትምህርት መረጃዎች ወደ ዲጂታል የመለወጥ ጅምር ሥራዎች መኖራቸውንም አስረድተዋል፡፡

ዩኔስኮ ግብዓቶችን በማሟላት ድጋፍ እንዲያደርግ መጠየቃቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

ስቴፋኒያ ጃኒኒ በበኩላቸው ዩኔስኮ ሀገሪቱ የትምህርት ዘርፉን በማሳደግ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የምታደርገውን ጥረት እየደገፈ መሆኑን ገልጸው÷ በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.