Fana: At a Speed of Life!

አፍሪካ ለዓለም ስልጣኔ በርካታ አስተዋጽኦ አበርክታለች – ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አፍሪካ ለዓለም ስልጣኔ በርካታ አስተዋጽኦ አበርክታለች ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

37ኛው የህብረቱ መሪዎች ጉባኤ የመክፈቻ ስነ-ስርዓት እየተካሄደ ይገኛል።

በጉባኤው መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ የአፍሪካ ህብረት በጂ20 የቋሚ አባልነት መቀመጫ ማግኘቱ አፍሪካ በዓለም ዓቀፍ መድረክ መደመጥ የሚያስችላትን ዕድል ፈጥሯል።

ይህም ሆኖ ግን አሁንም መመለስ ያለባቸው በጣም ወሳኝ ጥያቄዎች መኖራቸውን አንስተዋል።

በዓለም የሃይል አወቃቀር እኛ አፍሪካውያን ምን አይነት ሚና ይኖረናል? በኢኮኖሚው መስክ እንዴት ቁልፍ ሚና መጫወት እንችላለን? የሚሉት ጥያቄዎች ለመመለስ ታሪካችንን ማየት ይኖርብናል ሲሉ አስገንዝበዋል።

አፍሪካ የዘመናዊው የሰው ልጅ መነሻ ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ቀደምት የአፍሪካ ግዛቶች የፈጠራና የስልጣኔ ባለቤት መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተለይም በእርሻ ዘዴዎች፣ በመድሃኒት ዕጽዋት አጠቃቀም፣ በኪነ-ህንጻ ና ግንባታ የአፍሪካ አህጉር ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።

እነዚህ ጉዳዮች አፍሪካ ለዓለም ስልጣኔ ጠቃሚ መሆኗን እንደሚያሳዩም አስረድተው፤ አፍሪካ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂና በትምህርት ዘርፎች የጎላ አበርክቶ እንዳላት ተናግረዋል።

ይህ የአፍሪካ አስተዋጽኦ በቅኝ አገዛዝ የተነሳ መደነቃቀፉን ጠቅሰው፤ የቅኝ ገዢዎች ስትራተጂካዊ አቀራረብ የአህጉሩን መሰረታዊ እሴቶችን ማፍረስ ላይ ያነጣጠረ እንደነበረ ጠቅሰዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.