በቀጣዮቹ 9 ቀናት በአንዳንድ አካባቢዎች ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር ተጠቆመ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሚቀጥሉት ዘጠኝ ቀናት ለዝናብ መፈጠር አስተዋጽኦ የሚያደርጉ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች በአንጻራዊ ሁኔታ እንደሚጠናከሩ የትንበያ መረጃዎች አመላከቱ፡፡
በዚሁ መሠረት በልግ አብቃይ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያኙ ተገልጿል፡፡
በመካከለኛው፣ በሰሜን ምሥራቅ እና በደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎችም በአንዳንድ ቦታዎቻቸው ላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች አመላክተዋል፡፡
ኢሉአባቦር፣ ጅማ፣ ሁሉም የሸዋ ዞኖች፣ ምዕራብ አርሲና አርሲ ዞኖች፣ አዲስ አበባ፣ ምሥራቅ ጎጃም፣ የሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞኖች፣ የሰሜን ሸዋና የኦሮሚያ ልዩ ዞን፣ የሲዳማ ክልል ዞኖች፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፣ ከመደበኛ ጋር የተቀራረበ ዝናብ እንደሚኖራቸው ይጠበቃል፡፡
በጥቂት ቦታዎቻቸውም ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ መባሉን የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂመረጃ አመላክቷል፡፡
እንዲሁም ቡኖ በደሌ፣ ምዕራብ ጉጂና ጥቂት የቦረና ዞን፣ ምዕራብና ምሥራቅ ሐረርጌ ዞኖች፣ የደቡብ ጎንደር ዞን፣ የባሕር ዳር ዙሪያ፣ የዋግኽምራ ዞን፣ ዞን 1፣ ዞን 4፣ ዞን 3 እና ዞን 5፣ የደቡብ፣ የደቡብ ምሥራቅ እና የምሥራቅ ትግራይ ክልል ዞኖች፣ የሲቲ እና ጥቂት የፋፈን ዞኖች ቀላል መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ ተብሏል።