ቦርዱ በቀጣይ በሚከናወኑ ተግባራት ዙሪያ ከጠቅላይ መምሪያ ዕዙ ጋር ተወያየ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃፀም መርማሪ ቦርዱ በአማራ ክልል የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መራዘሙን ተከትሎ በቀጣይ በሚከሆኑ ተግባራት ዙሪያ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ጋር ተወያየ፡፡
በውይይታቸውም÷ ባለፉት ጊዜያት ለዕዙ የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች አፈፃፀም፣ አዋጁ ከተራዘመ በኋላ ያለው አሁናዊ ክልላዊ ሁኔታ በተለይም ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች እንዳይፈፀሙ ከመከላከል አኳያ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ መክረዋል፡፡
ክልሉን ወደ ሠላማዊ ሁኔታ ለማሸጋገር የተሠራው ሥራ አንፃራዊ ሠላም ማስገኘቱ እና ሠላሙን ለማፅናት አሁንም ቀሪ ሥራዎች መኖራቸው ተጠቁሟል፡፡
ቦርዱ ባለፉት ስድስት ወራት ወደ ክልሉ በማቅናት ክትትል ማድረጉን በውይይቱ ላይ ማንሳቱን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡
ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ በበኩሉ÷ በክልሉ የተመዘገቡና እየተመዘገቡ ያሉ የሠላም ጉዳዮችን፣ ከዚህ በፊት የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች የተፈፀሙትንና እየተፈፀሙ ያሉትን ጉዳዮች እንዲሁም መፈፀም ያለባቸው ተግባራትን በዝርዝር አቅርቧል፡፡