የጋምቤላ ክልል ም/ቤት መደበኛ ጉባዔ የተለያዩ ደንቦችና ሹመቶችን በማጽደቅ ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጋምቤለ ክልል ምክር ቤት 3ኛ የስራ ዘመን 5ኛ መደበኛ ጉባኤ የተለያዩ ደንቦችና ሹመቶችን በማጽደቅ ተጠናቅቋል።
የምክር ቤቱ አፈ- ጉባዔ ባንቻየሁ ድንገታ÷ አመራሩ ባለፈው ግማሽ ዓመት የተመዘገቡ ስኬቶችን በማስፋትና ጉድለቶችን በማረም በቀጣይ የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዝገብ ጠንክሮ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
በክልሉ በተደጋጋሚ የተከሰቱ የፀጥታ ችግሮች መነሻቸውን በመለየት መፍትሔ ለመስጠት በመንግስት የተወሰዱ የእርምት እርምጃዎች እና በፀጥታ አካላት የተቀናጀ ጥረት በሕዝቦች መካከል የተፈጠረውን አለመተማመንና ስጋቶች ለማስወገድ ጥረት መደረጉን ተናግረዋል።
በክልሉ የተሰሩ የልማት ሥራዎች አበረታች ናቸው ቢባልም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የግብርና ሥራዎችን ማዘመን በሚመለከት የሚቀሩ ሥራዎች በርካታ መሆናቸውን መንገንዘብ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።
የሕግ የበላይነትን ለማስከበር በፍርድ ቤቶችና በፍትሕ አካላት አካባቢ የሚታዩ የአፈፃፀም ክፍተቶችን ለመቅረፍ የተጀመረውን የፍርድ ቤቶች የፍትህ ትራንስፎርሜሽን እቅድ በአግባቡ ለመፈፀምና ለማስፈፀም የተቀናጀ ሥራ መስራት እንደሚጠይቅም አብራርተዋል።
“በተለይም አመራሩ የኑሮ ውድነት፣ የብልሹ አሰራር፣ የፕሮጀክቶች አፈጻጸም፣ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በቁርጠኝነት ሊሰራ የገባል” ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
ጉባዔው አቶ ኡጁሉ ኝጎዎን የክልሉ ምክር ቤት የሕግ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ በማድረግ ሲሾም የሶስት ዳኞችን ሹመትም አጽድቋል፡፡