በቀጣዮቹ ሳምንታት ከ1 ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ጂቡቲ እንደሚደርስ ተጠቆመ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በመጪዎቹ ሁለት ሳምንታት 1 ሚሊየን 274 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ጂቡቲ ወደብ እንደሚደርስ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን አመላከተ፡፡
ለ2016/17 የምርት ዘመን ከተገዛው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥም 510 ሺህ ኩንታል ዩሪያ የጫነች ‘አባይ ሁለት’ መርከብ ጂቡቲ መድረሷም ተጠቅሷል፡፡
እስከአሁንም 9 ሚሊየን 395 ሺህ 606 ኩንታል ማዳበሪያ ወደብ መድረሱን የኮርፖሬሽኑ መረጃ አመላክቷል፡፡
ከዚህ ውስጥም 8 ሚሊየን 731 ሺህ 403 ኩንታል ወደ ሀገር ውስጥ ተጓጉዞ በመሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበራት አማካኝነት ለአርሶ አደሮች እየቀረበ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በመጪዎቹ ሁለት ሳምንታትም 834 ሺህ ኩንታል ኤን ፒ ኤስ እና 440 ሺህ ኩንታል ዩሪያ በአጠቃላይ 1 ሚሊየን 274 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ጂቡቲ ወደብ እንደሚደርስ ይጠበቃል ነው የተባለው፡፡