በትራፊክ አደጋ የ7 ሰዎች ሕይወት አለፈ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን ሰዮ ወረዳ አላኩ አቦ ቀበሌ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የሰባት ሰዎች ሕይወት አለፈ፡፡
በተጨማሪም በ10 ሰዎች ላይ ከባድ እና በአራት ሰዎች ላይ ደግሞ ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን የዞኑ ኮሙኒኬሽን መምሪያ መረጃ ያመላክታል፡፡
ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችም በደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን የሰዮ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት የትራፊክ ደኅንነት አስተባባሪ ኢንስፔክተር ጌታሁን ነገሪ ተናግረዋል።
አደጋው የተከሰተው ከአንፊሎ ወረዳ 60 ኩንታል ቡና እና 30 ሰዎችን ጭኖ ወደ ደምቢ ዶሎ ከተማ ሲጓዝ የነበረ የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪ አላኩ አቦ ቀበሌ ላይ በመገልበጡ ነው ብለዋል።