በቀጣናው ድንበር ተሻጋሪ የሆኑ ወንጀሎችን መከላከልና መቆጣጠር መቻሉ ተገጸ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና አባል ሀገራት የፖሊስ ለፖሊስ ግንኙነትና ትብብርን በማጠናከራቸው ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን መከላከልና መቆጣጠር መቻሉን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ገለጸ፡፡
በፌደራል ፖሊስ ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሸነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ የተመራ ልዑካን ቡድን በቡሩንዲ ቡጁምቡራ እየተካሄደ በሚገኘው 48ኛው የምሥራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅት ቴክኒክ ኮሚቴዎች ጉባዔ ላይ እየተሳተፈ ነው፡፡
ጉባኤው “ሽብርተኝነትን እና ዓለም አቀፍ የተደራጁ ወንጀሎችን በመዋጋት ረገድ የሕግ አስከባሪ አካላት ትብብርን ለማጠናከር የቀጣናውን የፖሊስ አቅምን መጠቀም” በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሉ በጉባዔው ላይ እንደተናገሩት÷ የአባል ሀገራት የፖሊስ ለፖሊስ ግንኙነትና ትብብርን ለማጠናከርና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡
በዚህም ሽብርተኝነት፣ ሕገ-ወጥ የሰዎች፣ የገንዘብ፣ አደንዛዥ ዕጽና የጦር መሣሪያ ዝውውርን በመከላከል አጥፊዎችን ለሕግ በማቅረብ ረገድ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልፀዋል።
የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት ቴክኒክ ኮሚቴዎች ሊቀመንበርነትን የአንድ ዓመት የሥራ ዘመናቸውን በስኬት ያጠናቀቁት ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም ሊቀመንበርነቱን ለብሩንዲ ብሄራዊ ፖሊስ የምርመራ ዲፓርትመንት ኃላፊ ሜጀር ጀነራል ሮጀር ኒዲኩማ አስረክበዋል።
ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም ከቴክኒክ ኮሚቴዎቹ ጉባዔ ጎን ለጎን በጉባዔው እየተሳተፉ ከሚገኙት ከቻይና ልኡካን ቡድን አባላት ጋር የጎንዮሽ ውይይት ማድረጋቸውም ተገልጿል፡፡
በውይይታቸውም ÷በምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት እና በቻይና መንግስት መካከል በትብብር መስራት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ መምከራቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡