13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ውድድር በዛሬው እለት በይፋ ይከፈታል
አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋና የሚካሄደው 13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት አክራ በሚገኘው የጋና ዩኒቨርሲቲ ስፖርት ስታዲየም ይደረጋል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የጋና ፕሬዚዳንት ናና አኩፎ አዶ፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት፣ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የጤና፣ የሰብዓዊ ጉዳዮችና ማኅበራዊ ልማት ኮሚሽነር አምባሳደር ሚናታ ሳማቴ ሴሱማ እና ሌሎች የኮሚሽኑ አመራሮች ይገኛሉ ተብሏል፡፡
እስከ ፈረንጆቹ መጋቢት 14 የሚቆየው ውድደሩ በጋና ሶስት ከተሞች ማለትም አክራ፣ ኩማሲና ኬፕ ኮስት ከተሞች የሚካሄድ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በውድድሩ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑክ አስቀድሞ አክራ ገብቶ የተለያዩ ዝግጅቶችን እያደረገ ይገኛል፡፡
በየአራት ዓመቱ የሚካሄደው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ውድድር በፈረንጆቹ 2023 መካሄድ የነበረበት ቢሆንም በውድድሩ አዘጋጆች መካከል በነበረ የገበያ መብቶች አለመግባባት ወደ 2024 መዘዋወሩ ይታወሳል።