ጋቪ የክትባት ሽፋንን ለማሳደግ የቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለፀ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፉ የክትባቶች ጥምረት (ጋቪ) በኢትዮጵያ የክትባት ሽፋንን ለማሳደግ የሚያስችል የቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለፀ፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው ከጋቪ ዋና የሀገራት ዳይሬክተር ቶኩንቦ ኦሺን (ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ በኢትዮጵያ የክትባት ማቀዝቀዣ ሳጥን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል የ18 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ስምምነት በመንግስት እና በጋቪ መካከል ተደርጓል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታዋ በወቅቱ÷ በኢትዮጵያ ለሚደረገው ብሄራዊ የክትባት እቅድ አፈፃፀም መንግስት ያልተቆጠበ ድጋፉን ያደርጋል በማለት ገልጸው፤ ጋቪ በኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ለሚያደርገው ድጋፍ አመስግነዋል።
ቶኩንቦ ኦሺን (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ከክትባት ድጋፍ ጋር በተያያዘ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ሀገራት አንዷ መሆኗን ገልፀዋል፡፡
ተቋሙ ከተለያዩ ሀገራት መንግስታት ጋር በመተባበር የክትባት ሽፋንን ለማጠናከር የሚያስችለውን የጋራ ፋይናንስ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ማለታቸውን ከገንዘበብ ሚስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡