የስራ ባህላችንን በመቀየር አባቶቻችን ያስመዘገቡትን ጀግንነት በየደረጃው ልንደግመው ይገባል – አቶ ጥላሁን ከበደ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የስራ ባህላችንን በመቀየር አባቶቻችን ያስመዘገቡትን ጀግንነት በየደረጃው ልንደግመው ይገባል ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።
“ከተረጅነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ሉአላዊነት”በሚል መሪ ሀሳብ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተዘጋጀ ክልላዊ የንቅናቄ መድረክ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዲላ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
በንቅናቄ መድረኩ ላይ ርዕሰ መስተዳድሩ÷ በቁጭትና በእልህ የስራ ባህላችንን በመቀየር አባቶቻችን በተለያዩ መስኮች ያስመዘገቡትን ጀግንነት በየደረጃው ልንደግመው ይገባል ብለዋል፡፡
የስራ ባህልን በመቀየር ክልሉን ብሎም ሀገርን ለማበልጸግ የተያዘውን ራዕይ እውን ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በየደረጃው የሚገኘው አመራር የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት የሚመራውና የሚያገለግለው ህዝብ ከድህነት እንዲላቀቅ ማገዝ የዘወትር ተግባሩ ሊሆን እንደሚገባ ማስገንዘባቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡