Fana: At a Speed of Life!

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለ140 አቅመ ደካማና አካል ጉዳተኛ ወገኖች ቤቶችን አስረከቡ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሚሰሩ ልማቶች ሁሉ ለሰው ልጆች ተስፋ የሚሰጡ እና የኑሮ ጫናን የሚያቃልሉ ይሆኑ ዘንድ ሰው ተኮርነታችን በተግባር የሚገለጽ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

በመዲናዋ”በጎነት” በሚል ስያሜ የተገነቡ ሁለት ባለ 9 ወለል ዘመናዊ ሕንጻዎች እና የሥራ ዕድል መፍጠሪያ ማዕከላት ተመርቀው ለነዋሪዎች መተላለፋቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡

ቤቶቹ የተላለፉት በልደታ ክ/ከተማ በተለምዶ “ቆርቆሮ ሰፈር” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ለመኖር ምቹ ባልሆኑ ቤቶች ይኖሩ ለነበሩ አቅመ ደካሞች፣ አካል ጉዳተኞች፣ ማየት የተሳናቸው፣ ለተለያየ ማህበራዊ ችግር ለተጋለጡ እና በልማት ለተነሱ ነዋሪዎች መሆኑን አንስተዋል፡፡

የመኖሪያ ቤቶቹ ሳሎን፣ መኝታ ቤት፣ የማብሰያ እና የመጸዳጃ እንዲሁም የመኝታ ክፍሎች ያላቸው ዘመናዊ ቤቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በመኖሪያ መንደሩ ከተላለፉት የመኖሪያ ቤቶች ጋር በማቀናጀት የእናቶችን ጫና የሚያቀል የህጻናት ማቆያ፣ ለአካባቢው እናቶች የስራ ዕድል የሚፈጥር ዘመናዊ የእንጀራ መጋገሪያ፣ የወንዶችና የሴቶች የውበት ሳሎኖችን እንዲሁም የልብስ ስፌት ማሽኖች ተዘጋጅተው ለነዋሪዎቹ የስራ እድል መፈጠሩን ተናግረዋል ።

በመኖሪያ መንደሩ ቤት ለተሰጣቸው ማየት የተሳናቸው ነዋሪዎችም ለእንቅስቃሴ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ኬኖች፣ ለአካል ጉዳተኛ ነዋሪዎች ደግሞ ክራንችና ዊልቸሮችን ስጦታ መበርከቱንም ጠቅሰዋል፡፡

ከንቲበዋ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመተባበር ቤቶቹን ለገነባው ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.