የታዳሽ ኢነርጂ ለአየር ንብረት የማይበገር ኢንዱስትሪን በማሳደግ የኢኮኖሚ እድገትን ያፋጥናል – ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ፤ ኢ/ር)
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የታዳሽ ኢነርጂ ሃብቶችን በመጠቀም የአፍሪካ የኢነርጂ እጥረትን ከመቀነስ ባሻገር ለአየር ንብረት የማይበገር ኢንዱስትሪ እንደሚያሳደግና የኢኮኖሚ እድገት እንደሚያፋጥን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ፤ ኢ/ር) ገለጹ፡፡
‘’የተፋጠነ አጋርነት ለታዳሽ ኢነርጂ ልማት በአፍሪካ’’ በሚል መሪ ሃሳብ የምክክር መድረክ ተካሄደ።
በመድረኩ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ፤ ኢ/ር) ፥ የታዳሽ ኢነርጂ ፍላጎትን ለማሳደግ በፈረንጆች መስከረም 2023 በናይሮቢ ኬንያ የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ መጀመሩን አስታውሰዋል፡፡
ለዚህም በተፋጠነ አጋርነት ታዳሽ ኢነርጂ በአፍሪካ ለማራመድ ቁርጠኛ የሆኑ ዓለም አቀፍ ሀገራትና ባለድርሻ አካላት መተባበራቸውን ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም ፥ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውሃ፣ የንፋስና የጸሀይ ሀይል አቅም እንዳላት ገልፀው፤ ምክክሩ ከዓለምአቀፍ የታዳሽ ኢነርጂ ኤጀንሲ ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ መዘጋጀቱ የሀገርን የኢነርጂ ሽግግርን ለማሳለጥ ጠቃሜታው የጎላ ነው ብለዋል።
አያይዘውም ፥ የታዳሽ ኢነርጂ ሃብቶችን በመጠቀም የአፍሪካ የኢነርጂ እጥረትን ከመቀነስ ባሻገር ለአየር ንብረት የማይበገር ኢንዱስትሪ ለማሳደግ እና የኢኮኖሚ እድገት ለማፋጠን እንደሚያስችልም ነው የተናገሩት።
አፍሪካ ያላትን ከፍተኛ የታዳሽ ኢነርጂ ሃብት ክምችት ለመጠቀም የሚያስችል የተመቻቸ የኢንቨስትመንትና የፋይናንስ አቅርቦት ውስንነቶች ምክንያት የ2063 አጀንዳ ለማስፈጸም ተግዳሮት መሆኑንም አንስተዋል።
የኢነርጂ አጋርነት ለማጠናከር ድጋፍ ያደረጉት የዴንማርክ፣ የጀርመን፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትሰ፣ የአሜሪካ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ማመስገናቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።