Fana: At a Speed of Life!

የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ከመልክዓ ምድሩ ጋር ተሰናስሎ የሀገር ባህልንና የተፈጥሮ ሃብትን ጠብቆ የተገነባ አስደናቂ ስፍራ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ከመልክዓ ምድሩ ጋር ተሰናስሎ የሀገር ባህልንና የተፈጥሮ ሃብትን ጠብቆ የተገነባ ከፍተኛ የቱሪዝም ሃብትና አስደናቂ ስፍራ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ረዳት ዋና ፀሐፊ እና የሰብአዊ እርዳታ አስተባባሪ ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ/ር) ተናገሩ።

የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ግንባታ ተጠናቅቆ ትናንት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) መመረቁ ይታወቃል።

በምረቃ ስነ-ስርአቱ ላይ ከተገኙት ታዳሚዎች መካከል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ረዳት ዋና ፀሀፊ እና የሰብአዊ እርዳታ አስተባባሪ ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ/ር) በፕሮጀክቱ አሰራር ተደንቄያለሁ ብለዋል።

ጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት በሚያስደምምና በሚያስደንቅ ጥበብ የተገነባ መሆኑን ጠቅሰው ይህም ለኢኮቱሪዝም ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል።

ጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ከመልክዓ ምድሩ ጋር ተሰናስሎ የሀገር ባህልንና የተፈጥሮ ሃብትን ጠብቆ የተገነባ አስደናቂ ስፍራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከግንባታው ጀምሮ በቀጣይም በአገልግሎቱ የአካባቢውን ነዋሪዎች የስራ እድል ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑንም አድንቀዋል።

በቀጣይም የበርካታ ጎብኚዎች መዳረሻ በመሆን በቱሪዝም ዘርፉ ከፍተኛ ሀብት መፍጠር የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው የሀገር ባህልን ከማስተዋወቅ ባለፈ ለቱሪዝም ዘርፍ ጥሩ መሰረት የጣለ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ የቱሪዝም ልማት የአረንጓዴ አሻራ የአካባቢ ጥበቃን መሰረት ያደረገ በመሆኑ በዓለም የአየር ንብረት ተጽእኖን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት በሚታይ ውጤት የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች ነው ብለዋል።

በተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (ዩኒዶ) የሥርዓተ-ፆታ እኩልነትና የሴቶች ማብቃት ዘርፍ ዳይሬክተር ኦሬሊያ ፓትሪዚያ ካላብሮ በበኩላቸው÷ የጎርጎራ ግራንድ ሪዞርት የተሰራበት ቦታና የመሬቱ አቀማመጥ የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ የጣና ሃይቅን ባማከለ ድንቅ የተፈጥሮ አቀማመጥን መሰረት አድርጎ የተሰራ በመሆኑ የትኛውም ቱሪስት ሊጎበኘው የሚመኘው መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥረትና ክትትል የተገነባ ዘመን ተሻጋሪ የሀገር ሃብት መሆኑንም ተናግረዋል።

የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት በተለይም ሴቶችን የስራ እድል ተጠቃሚ በማድረግና በማገዝ የዜጎችን ተጠቃሚነት መሰረት ያደረገ መሆኑ የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡

ከኬኒያ የመጡት አንድሪው ምቦጎሪ፤ የጎርጎራ ግራንድ ሪዞርት ሁላችንም የምንኮራበት እጅግ አስደናቂ ፕሮጀክት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ከፕሮጀክቱ በጣና ሃይቅ ተቃራኒ ያለው እይታ የሚማርክ፣ ባህል፣ ታሪክንና ዘመናዊነትን አጣምሮ የያዘ መጎብኘት ያለበት ድንቅ ስፍራ መሆኑንም ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.