በሕገ-ወጥ መንገድ ነዳጅ ሲሸጡ ነበር የተባሉ 22 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሕገ-ወጥ መንገድ ነዳጅ በመደበቅ ሲሸጡ ነበር ያላቸውን 22 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የሐረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ግለሰቦቹ በሐረር ከተማ በሕገ-ወጥ መንገድ ነዳጅ ሲሸጡ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን በኮሚሽኑ የወንጀል ምርመራ ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ረመዳን ጅብሪል ተናግረዋል፡፡
በሁሉም ወረዳዎች በተደረገው ጥናት 1 ሺህ 518 ሊትር በጄሪካን እና በፕላስቲክ ጠርሙሶች የተሞላ ነዳጅ ተይዟል ማለታቸውን የኮሚሽኑ መረጃ አመላክቷል፡፡
የነዳጅ ማደያዎችም በዚህ ሕገ-ወጥ የነዳጅ ንግድ እጃቸው እንዳለበት በመግለጽ በቀጣይ ተገቢው ማጣራት ከተደረገ በኋላ ሕጋዊ ርምጃ እንደሚወሰድ አረጋግጠዋል፡፡
የቁጥጥር እና ክትትል ሥራውም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያመላከቱት፡፡