በአማራ ክልል ችግሮችን በመቋቋም ሕዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ሥራዎች ተከናውነዋል – አቶ አረጋ ከበደ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ችግሮችን በመቋቋም በሁሉም ዘርፎች ሕዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ውጤታማ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ፡፡
አቶ አረጋ የአስፈፃሚ አካላትን የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ለክልሉ ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት÷ የክልሉን ሰላም ወደነበረት ለመመለስና ልማቱን ለማፋጠን ዘርፈ-ብዙ ተግባራትን ማከናወን ተችሏል ብለዋል።
ከተከናወኑት መካከልም የግብርና ዘርፉ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው÷ ለዚህም በ2015/2016 የምርት ዘመን በተለያየ ሰብል ከለማው መሬት 145 ሚሊየን ኩንታል ምርት መገኘቱን ጠቅሰዋል።
እንዲሁም በበጋ ወራት በመስኖ ከለማው 299 ሺህ ሔክታር ከአንደኛ ዙር 29 ሚሊየን ኩንታል ምርት በማግኘት በገበያ የአቅርቦት ክፍተቱን መሸፈን እንደተቻለ ገልጸዋል።
በተያዘው የመኸር ወቅትም 5 ነጥብ 1 ሚሊየን ሔክታር በተለያየ ሰብል በማልማት 169 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ የእርሻና የዘር ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በሌላ በኩል የሥራ አጥነት ችግርን ለማቃለል በተደረገው ጥረት በበጀት ዓመቱ ከ522 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች የሥራ ዕድል በመፍጠር በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን በሪፖርታቸው አመላክተዋል።
የክልሉን የኢንቨስትመንት ፍሰት ለማሳደግ በተከናወነው ሥራም 2 ሺህ 260 ባለሃብቶች በተለያዩ የልማት ዘርፎች ለመሰማራት የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን አስታውቀዋል።
በማዕድን ዘርፍም 20 ሺህ 623 ኪሎ ግራም የኦፓል ምርት ለገበያ ቀርቦ ገቢ መገኘቱን የገለጹት አቶ አረጋ÷ በመንገድ ልማት ዘርፍም 331 ኪሎ ሜትር መንገድ በአዲስ በመገንባት 109 ቀበሌዎችን እርስ በርስ ማገናኘት ተችሏል ብለዋል፡፡
በቀጣይም ቀደም ሲል የተገኙ መልካም ልምዶችን በማጠናከርና ክፍተቶችን በማስተካከል ሕዝቡ የዘላቂ ሰላሙ ባለቤት እንዲሆን ከማድረግ ጎን ለጎን የልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ሁሉም በቁርጠኝነት እንዲንቀሳቀስ አሳስበዋል፡፡