115 ኩንታል አደንዛዥ እጽን ጨምሮ ሕገ-ወጥ ምርቶች በቃጠሎ ተወገዱ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 115 ኩንታል ኮኬን፣ ካናቢስ፣ ሔሮይን እና የተለያዩ አደንዛዥ እጾችን ጨምሮ ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶች፣ ለሕገ-ወጥ ተግባር ሊውሉ የነበሩ ፓስፖርቶች እና በኮንትሮባን የገቡ ምርቶች በቃጠሎ መወገዳቸው ተገለጸ፡፡
የተቃጠሉት ምርቶች ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ መያዛቸውን እና የማስወገድ ሥራውም በፍርድ ቤት ውሳኔ መሠረት መከናወኑን በፌደራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ የእጽ አስወጋጅ ኮሚቴ አባል ኮማንደር በለጠ ጌታቸው አስታውቀዋል፡፡
ምርቶቹ የተያዙት በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያና በአዲስ አበባ ሁሉም መግቢያ በሮች ላይ በተደረገ ፍተሻ መሆኑን ጠቅሰው÷ ምርቶቹ ወደ ማኅበረሰቡ ቢገቡ ኖሮ የከፋ ጉዳት ከማድረስ ባለፈ ወንጀል ያስፋፉ ነበር ብለዋል።
እየተደረገ ባለው ጥብቅ ፍተሻ ምክንያት ወደ አዲስ አበባ የሚገቡ አደንዛዥ እጾችና የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መቀነሳቸውንም አመላክተዋል፡፡
በዘመን በየነ